በሲዳማ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል- አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል- አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ፤የካቲት 01/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ባለፉት ዓመታት ተፋሰስን መሰረት በማድረግ በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የዘንድሮውን የተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በቦርቻ ወረዳ ተገኝተው በይፋ በማስጀመር ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የዘርፉ ሥራዎች ውጤት ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በክልል ደረጃ እየተከናወነ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ በቂ ባይሆንም የደን ሽፋንን እና የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ እስችሏል።
በተለይ ገላጣ የነበሩ ሥፍራዎች በዕፅዋት በመሸፈናቸው፣ የአፈር ለምነትና ዕርጥበትም በመሻሻሉም ሞቃታማ የነበሩ አካባቢዎች የአየር ንብረታቸው እየተስተካከለ ምቹ ሁኔታ መፈጠራቸውን ገልጸዋል።
ለዚህ ማሳያው የቦርቻ ወረዳ አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ከመራቆታቸው የተነሳ አፈራቸው ተሸርሽሮ ድንጋይ ብቻ ይታይባቸው የነበሩ ሥፍራዎች ከስድስት ዓመታት በኋላ አገግመው በዛፍና ሌሎች ዕፅዋቶች ተሸፍነው ለማየት መብቃታቸውን አስረድተዋል።
የተፋሰስ ልማት ሥራ ለአፈርም ሆነ ለአየር ንብረት መሻሻል ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን የአይን እማኝ መሆን ችለናልም ብለዋል ፡፡
የዘንድሮው ሥራ በ 546 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ እንደሚከናወን ጠቁመወ ው በዚህም 100 ሺህ 275 ሄክታር በላይ እንደሚለማ ተናግረዋል።
የለማው መሬት ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር ክፍተቶች እንዳለ ገልጸው በዚህ ረገድ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን አስታውቀዋል።
በተለይ ሥራ አጥ ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎች ልማቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ላይ ንብ በማነብና የእንስሳት መኖ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው በክልሉ እስካሁን 216 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህም አረንጓዴ ሥፍራዎችን መፍጠር ከመቻሉም በላይ በንዑስ ተፋሰሶቸ ላይ ለመስኖ የሚሆኑ ጅረቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ በሚካሄደው ት ሥራ 1 ሚሊዮን 250 ሺህ ሰዎች ለ30 ቀናት እንደሚሳተፉ የተናገሩት ኃላፊው ይህንን ሥራ ለማቀላጠፍ 250 ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።
ልማቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የተቀናጀ የሰው ኃይል አጠቃቀምና የሥራ ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የሀዋሳን ሐይቅ እንዲሁም በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ላይ የተገነባውን የጊዳቦ መስኖ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ የሚያስችሉ የሥነ አካላዊ ሥራዎችም በዙሪያቸው ባሉ ወረዳዎች ላይ በትኩረት እንደሚከናወኑም እንዲሁ።
በሥነ አካላዊ ሥራው የለማውን መሬት በሥነ ሕይወት ለመሸፈንም ለመጨው ክረምት ተከላ 120 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑንም አመልክተዋል።
በልማት ሥራው እየተሳተፉ ካሉት መካከል አርሶ አደር ኢብራሂም ማሞ በሰጡት አስተያየት በፊት አካባቢያቸው በመራቆቱ ማሳቸው ምርት መስጠት ከማቆሙም ሌላ ለእንስሳት የሚሆን ሣር ለማግኘትም ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
መንግስት ህዝቡን ያሳተፈ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ከጀመረ ወዲህ መሬታችን ጥቅም መስጠት ጀምሯል ያሉት አርሶ አደሩ አልመተው ከንክኪ ጠብቀው ካቆዩት ሥፍራ ላይ ለመኖ እንዲሁም ለቤት ክዳን የሚሆን ሳር እያገኙ ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።
አርሶ አደር አሰፋ ሄላ በበኩላቸው መሬታቸው ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ እርጥበት መያዝ በቻሉን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ብዙ በረከቶችን እያየን ነው ያሉት አርሶ አደሩ ለእንስሳቶቻቸው መኖ ከማግኘታቸውም ባለፈ አካባቢያቸው የዱር እንስሳትና አዕዋፍ መጠጊያ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።
አሁን ላይ በተፋሰስ ልማት ላይ የምንሳተፈው ጥቅሙን ስላወቅን ስለሆነ በራሳችን ፍላጎትና ተነሳሽነት ነው የምንሰራው ብለዋል።