ቀጥታ፡

በመጪው አገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራሁ ነው -- የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት

ጥር 1/2013 (ኢዜአ) በመጪው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ገለጸ።

ቅንጅቱ በመንግስታቱ ድርጅት በጾታ እኩልነትና በሴቶች አቅም ማጎልበት ላይ ከሚሰራው /ዩ.ኤን ውሜን/ ጋር በመሆን በመጪው ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ በሚያሳድግበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል።

የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን ምርጫው በመቃረቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው መጠናከር አለበት ብለዋል።

ቅንጅቱ ቀደም ሲል ለስራው የሚያግዙ ዝግጅቶች ሲያደርግ መቆየቱንና አገራዊ ምርጫው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በመራዘሙ እንቅስቃሴው መገታቱን ተናግረዋል።

ይሁንና አሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ያረጋገጠ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተያያዘም የሴቶች ጉዳይ የምርጫ አጀንዳ እንዲሆን እየተቀሰቀሰ መሆኑን አክለዋል።

ቅንጅቱ የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ የስልጠና መመሪያዎችን በማዘጋጀት በየክልሉ የአሰልጣኞች ስልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሻሻሉ ግብዓት በመስጠትና ሴቶች በፖለቲካው መስክ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ  ከምርጫ ቦርድ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በጾታ እኩልነትና በሴቶች አቅም ማጎልበት ላይ የሚሰራው ዩ.ኤን ውሜን የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ተወካይ አና ፓሪኒ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ሴቶችን ለማብቃት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

በቀጣይ ቅንጅቱ ሴቶችን ለማብቃት የሚያደርጋቸውን የትምህርት፣ የቴክኒክና ተሞክሮዎችን የማካፈል እንቅስቃሴ እንደሚያግዙም ገልፀዋል።

በውይይቱ ከአገር ውስጥና ከባህር ማዶ የተውጣጡ የሴቶችና የሲቪል ማኅበራት ሴቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ያግዛሉ ያሏቸውን ተሞክሮዎች በበይነ መረብ አካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም