ዓለም አቀፍ የቡና ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊከበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የቡና ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊከበር ነው
አዲስ አበባ ሃምሌ 18/2010 ዓለም አቀፍ የቡና ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሊከበር መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ። የቡና ቀኑ በቀጣይ ህዳር 2011 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል። የቡና ቀኑ አከባበር ዋና አስተባባሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝግጅቱን በተመለከተ እቅዱን ለባለድርሻ አካላት ትናንት ይፋ አድርጓል። " በምድረ ቀደምት የቡና ውብ ጣዕም ይቅመሱ" በሚል መሪ ቃል ነው በዓሉ የሚከበረው። በዓሉ በዓለም ላይ ያሉ የቡና አምራቾች፣ ላኪዎች፣ አጥኚዎች፣ ጻሓፊዎች እንዲሁም ቡና አፍቃሪዎችን የሚያገናኝ ይሆናል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም "ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር እና ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀች እንደመሆኗ ዓለም አቀፍ የቡና ቀን በኢትዮጵያ መካሄዱ ተገቢ ነው" ብለዋል። "የዓለም አቀፍ የቡና ቀን መከበር የአገራችንን የተፈጥሮ ቅርሶች ለዓለም ለማስተዋወቅና በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ እያደረግን ያለው ጥረት አንዱ አካል ነው" ሲሉም አቶ ተወልደ ተናግረዋል። ዓለም አቀፍ የቡና ቀኑ የሚዘጋጀው በኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን፣ በኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር፣ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት እና የዘርፉ ባለድርሻዎች፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በንግድ ሚኒስቴር የጋራ ትብብር ነው። ዝግጅቱ አውደ ርዕይ፣ ውይይትና የቡና መገኛ በሆነችው ከፋ ጉብኝት ማድረግን ያካትታል። ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ባለድርሻ አካላትን በአንድ የሚያገናኝና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚሆንም አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።