በዞኑ በ120 ሚሊየን ብር የትምህርት ቤቶችን የግንባታ ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በ120 ሚሊየን ብር የትምህርት ቤቶችን የግንባታ ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተካሄደ ነው
ደሴ የካቲት 1/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን በ120 ሚሊዮን ብር የትምህርት ቤቶችን የግንባታ ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል አበጋዝ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ካሉ 1 ሺህ 210 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 83 በመቶው ግንባታቸው ከደረጃ በታች ነው።
"የትምህርት ቤቶች የግንባታ ደረጃ አለመጠበቅ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ግቡን እንዳይመታ ጫና አሳድሯል" ብለዋል ።
የትምህርት ቤቶችን የግንባታ ደረጃ ለማሻሻል ከአማራ ልማት ማህበርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በፈጀ ወጭ ሁለት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ ስምንት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንበተው በዚህ አመት አገልገሎት ላይ አንዲውሉ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
በዚህ አመት በተለያዩ ወረዳና ከተሞች በትምህርት ቤቶች ከ120 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ 240 መማሪያ ክፍሎች ያላቸው የ60 ህንጻዎች ግንባታ ተጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
የሌሎች የሦስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ለማካሄድ መሰረተ ድንጋይ መቀመጡን ጠቁመው የትምህርት ቤቶቹን ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በተያዘ አቅጣጫ መሰረት አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እደሚደረግ አስታውቀዋል።
"በከተማው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማስጠበቅ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላት በማስተባበር በነባር ትምህርት ቤቶች ከ10 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ 24 መማሪያ ክፍል ያሏቸው የስድስት ህንጻዎች ግንባታ ተጀምሯል" ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ሁሴን ናቸው ።
በተጨማሪም በ11 ሚሊዮን ብር ለሚገነባ አንድ አዲስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት መሰረተ ድንጋይ መቀመጡን ጠቁመው የትምህርት ቤቱ ግንባታ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመር አመላክተዋል።
የአማራ ሳይንት ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ መኮንን ገንብረው በበኩላቸው
በወረዳው 100 አንድኛ ደረጃና ሦስት 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች መኖራውን ጠቁመው በ50 ትምህርት ቤቶች የማስፋፊያና እድሳት እንዲሁም ቁሳቁስ የማሟላት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ።