ዜጎች በመጪው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ መፍጠሪያ ተግባራት መጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች በመጪው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ መፍጠሪያ ተግባራት መጠናከር አለባቸው
የካቲት 1 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በመጪው 6ኛ አገራዊ ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እንዲጠናክሩ መከረ።
ማኅበሩ ምርጫ ነክ ጉዳዮች በሕግ አግባብ እንዲከናወኑ የበኩሉን እንደሚወጣም አስታውቋል።የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ፊሊጶስ አይናለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ በሚኖሩ ሁነቶች ማኅበሩ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው።
ሕዝቡ ሕገ-መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ በምርጫው እንዲሳተፍ የምርጫ ዓላማ፣ ግብና ጥቅም ላይ ግንዛቤ ለማስያዝ እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።
ምርጫ የዜጎች ዋነኛ ዴሞክራሲያዊ መብት መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ "ይህን መብት በአግባቡ ተጠቅሞ የሕግ የበላይነትና ሠብዓዊ መብት እንዲከበር የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባዋል" ብለዋል።
በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም አማራጭ ሐሳቦችና ፖሊሲዎቻቸውን በተደራጀ መንገድ ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ መክረዋል።
በዚህም ዜጎች በሚሰጡት ድምጽ የሚያስተዳድራቸውን አካል የሚመርጡበት መሆኑን ተረድተው መብታቸውን በትክክል መጠቀም እንደሚችሉ አብራርተዋል።
መራጩ ሕዝብ ከምርጫ በፊት በቂ ግንዛቤ እንዲይዝ መቀስቀስ፣ ዜጎች ነጻ ሆነው እንዲመርጡ ማድረግና ውጤቱን በሕግ አግባብ መቀበል ወሳኝ ጉዳዮች እንደሆኑም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ፊሊጶስ ገለጻ፤ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አማራጭ ሃሳቦችና ፖሊሲዎች ተመስርቶ ሕዝብ በሚሰጣቸው ድምፅ የሚያገኙትን ውጤት አክብረው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።
ማኅበሩ ከምርጫ በኋላ አለመግባባቶች ቢፈጠሩ በሕግ አግባብ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዕቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል።