ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የማጠናከር ዓላማ የያዙ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች መቀሌ ገቡ

የካቲት 1/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የማጠናከር ዓላማ የያዙ ከሁሉም የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች መቀሌ ገቡ፡፡

በራሳቸው ፈቃድና በሠላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ወደ መቀሌ የተጓዙት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአባቶቹ ወደ መቀሌ መምጣት በትግራይ ክልል ሕዝቡ በመተሳሰብ አብሮ እንዲኖር ለማድረግ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ 

በተጨማሪም የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር እንደቀደመው ሁሉ በፍቅር እንዲኖር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ የውጭ ጉዳይ የበላይ ሃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዲሁም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ እድሪስና ሌሎች የእምነት ተቋማት አባቶችም መቀሌ ገብተዋል፡፡

ከአገር ሽማግሌዎችም ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ሌሎችም በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 

የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎቹ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት በህወሓትና በመንግስት መካከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ወደ መቀሌ አቅንተው በህወሓት ቡድን እምቢተኝነት መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ 

በመቀሌ ለሁለት ቀናት ቆይታ የሚያደርጉት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ መቀሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የከተማዋ ከንቲባና የጊዜያዊ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም