ሀገራዊ ለውጡን በባለቤትነት እናስቀጥላለን... የወላይታ ሶዶ ዞን ነዋሪዎች

43

ሶዶ፤ የካቲት 1/2013 (ኢዜአ) የሀገራዊ ለውጡ ደጋፊ ብቻ ሳንሆን ባለቤት ለመሆን እንሰራለን ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ ።

ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ያላቸውን ድጋፍ ዛሬ በሶዶ ስታድየም ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል ።

ሰልፈኞቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የጁንታውን ቡድን ለማምከን የሰጡትን በሳል አመራር እናደንቃለን፣ አደናጋሪ አሉባልታዎችን በማክሸፍ ለለውጡ እንተጋገን፣ ታላቁ የለውጥ ጉዟችን በዶክተር አበይ አህመድ መሪነት ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማሰማት ድጋፋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ከሰልፈኞቹ መካከል የዳሞት ፑላሳ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ታደለች አርካ በሰጡት አስተያየት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር እየተመዘገቡ ላሉ ድሎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

“ፈተናዎችን በጋራ እየመከትን የለውጡን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን ለመቆም ዝግጁ ነን “ ብለዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባከናወኗቸው ተግባራት በተገኙት ድሎች ኩራት ተሰምቶናል” ያሉት ደግሞ የዞኑ የሀገር ሽማግሌ አቶ ሰይፉ ለታ ናቸው።

"የተገኘው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ያሉት አቶ ሰይፉ ፈተናዎችን በስራና በጋራ በመመከት ለውጡን ለማስቀጠል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከሚመሩት መንግስት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል ።

ነዋሪዎቹ የለውጡ ደጋፊ ብቻ ሳይሆኑ ባለቤት ለመሆን እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ በወቅቱ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ጠንካራ አመራር በጁንታው ቡድን ላይ የተገኘው ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተባብረው ከተነሱ የማይወጡት ችግር እንደሌለ ማሳያ ነው።

"የአንድነትና የአብሮነት ሀገር የሆነችውን የኢትዮጵያ ገፅታ ለማጉላት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ የሚጠይቅበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው መላው ህዝብ ለስኬታማነቱ ሊነሳ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን በተባበረ ክንድ በማሸነፍ ግንባታውን መጨረስ እንደሚቻልም ገልጸው፤ የግድቡ  ግንባታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የሶዶ ከተማ ከንቲባ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ፀጋዬ በበኩላቸው "አንዳንድ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ በመንግስትና ህዝብ መካከል ቅራኔ የሚፈጥሩ ግለሰቦችንና ቡድኖች ዓላማ መዘንጋት የለበትም" ብለዋል።

የወላይታን ህዝብ መልካም እሴት ለማጠልሸት በተለይ በማህበራዊ ትስስሮች ላይ ሀሰተኛ መረጃዎች የሚያሰራጩ እንዳሉ ያመለከቱት ኃላፊው፤ ህብረተሰቡ ለሀገሪቱ ልማት በሚጠቅሙ አጀንዳዎች ላይ  ብቻ በማተኮር የበኩሉን ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም