የአማራ ክልል ዓመታዊ የባህል ስፖርት ውድድር ተጀመረ

92

ደሴ፤ የካቲት 1/2013(ኢዜአ) የአማራ ክልል ከ800 የሚበልጡ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ዓመታዊ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ተጀመረ።

የክልሉ  ስፖርት ኮሚሽነር  አቶ ባዘዘው ጫኔ ውድድሩ ትናንት ሲጀመር  እንደገለጹት እስከ የካቲት 8/2013 ዓ.ም. በሚቆየው ውድድር  ገና፣  ገበጣ፣  ትግል፣  ፈረስ ጉግስን ጨምሮ በ11 ዓይነት የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄድ ሲሆን፤ ስፖርተኞቹ ከ14 የክልሉ ዞኖች የተወጣጡ ናቸው።

በባህላዊ ስፖርት ተተኪ ትውልድ ለማፍራት በየዓመቱ ውድድር እንደሚካሄድ ጠቅሰው ባህልና ወግ ከማሳደጉም ባለፈ አንድነትንና አብሮነትን  ለማጎልበት ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። 

የውደድሩ ዓላማም በሀገር አቀፍ ደረጃ በድሬደዋ ከተማ ለሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንደሆነ  ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ስፖርት ተጠሪ ጽህፈት ቤት የስፖርት ውድድሮች ቡድን መሪ አቶ ፀጋዬ ለገሰ በበኩላቸው ዞኑ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ቅደመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በአስር የስፖርት ዓይነቶች የሚሳተፉ ከ50 በላይ ስፖርተኞች ልምምድ ሲያርጉ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ጥሩ ውጤትም እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ  ውድድሩ ኢትዮጵያዊ ባህሉን ጠብቆ በስፖርታዊ ጨዋነት በሠላም እንዲጠናቀቅ ዞኑ አስፈላጊውን ቅደመ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

ባህላዊ ስፖርቶች  ባህል፣ ወግና እሴቶች ከማስቀጠላቸውም ባለፈ በአካባቢው ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በምንሳተፍበት  የገና ጨዋታ ጥሩ ውጤት ለማምጣት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረጋቸው የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ የገለጸው ደግሞ  የደቡብ ወሎ ዞን ወክሎ በገና የሚወዳደረው ወጣት አህመድ አሊ ነው፡፡

የቀደምት አባቶችን የባህል ጨዋታ ከማስቀጠላችንም ባለፈ በየዓመቱ በሚካሄዱት ውድድር አንድነታቸውን  አጠናክረው የአካባቢያቸውን ሠላም ለመጠበቅ እያገዘ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርት ውድድሮችና ፌስቲቫል ከየካቲት 21 /2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት  በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም