የአካባቢያቸውን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚጥሩ የሮቤ ከተማ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያቸውን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚጥሩ የሮቤ ከተማ ወጣቶች ገለጹ
ጎባ ሀምሌ 18/2010 ለአካባቢያቸው ደህንነት ዘብ በመቆም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የበኩላቸወውን ጥረት እንደሚያደርጉ በባሌ የሮቤ ከተማ ወጣቶች ገለጹ፡፡ የከተማዋ ወጣቶች ሰሞኑን በጎባ አካባቢ በተቀሰቀሰው ግጭትና በሰላም ዙሪያ ዛሬ ከመንግስት አካላት ጋር ተወያይተዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት በከር አደም በሰጠው አስተያየት " እኛ ወጣቶች በሃገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ውስጥ ሚናችንን ልናጠናክር ግድ ሊለን ይገባል" ብሏል። በቅርቡ በአከባቢያቸው ተከስቶ በነበረው ግጭት በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገልፆ እንዲህ አይነቱ ድርጊት እንዳይደገምና በአካባቢው ሰላም ለማስፈን የሚደረገውጥ ጥረት እንደሚያግዝ ተናግሯል። በቅርቡ በጎባ ከተማ በተፈጸመው ግጭት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ የአካባቢውን ወጣት የማይወክል መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዟል። በከተማዋ በየደረጃው የተደራጁ ቄሮዎች አንድነታቸውን አጠናክረው ከኃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከአባገዳዎች ጋር በመሆን ለአካባቢው ሰላም ዘብ በመቆም አጥፊዎችን አጋልጦ ለህግ ማቅረብ እንዳላባቸውም አመልክቷል። ወጣት ጥለሁን መንግስቱ በበኩሉ ተከስቶ በነበረው ችግር በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው ጉዳት እንዳሳዘናው ገልፆ "ቄሮ ጸጥታ የሚያደፈርሱ ኃይሎችን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ ለሰላሙ ዘብ መቆም አለበት" ብሏል። በከተማው በተከሰተው ግጭት በባሌ ህዝብ መካከል የኃይማኖት ግጭት እንደለ የሚነፈሰው ወሬ ሰላም ወዳዱን የአካባቢውን ህዝብ እንደማይወክል ገልጿል፡፡ መንግስት ወጣቱን ስሜታዊ እንዲሆን በማድረግ ለራሳቸው እኩይ ተግባር የተጠቀሙበትን የከሰሩ ኃይሎችን ሴራ አጣርቶ ለህግ ማቅረብ እንዳለበት ጠይቋል። ቄሮዎች በሀገሪቱ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት እንዲሰፍን በመታገል አኩሪ ገድል መፈጸማቸውን የተናገረው ደግሞ ሌላው የውይይት መድረኩ ተሳታፊ ወጣት አህመድ ሱልጣን ነው። "የቄሮ መዋቅርን በጥርጣሬ አይን የሚያዩና የመደመር እሳቤ ያልገባቸው ያልተደሱ አመራሮች ልፈተሹ ይገባል " ብሏል። ወጣቱ ኃይልም ከስሜታዊነት በመራቅ በስሙ የሚነግዱትን ግለሰቦችን ከውስጡ በመለየት ለህግ እንዲቀርብ በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለበትም አመልክቷል። በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ወጣቶቹ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦህዴድ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው የክልሉን ህዝብ ከድህነት ለማላቀቅ መንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። "ወጣቱም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን ከሚያደርገው ጥረት በሻገር ለህዝቦች አንድናትና አብሮነት ተገቢ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል። ወጣቱ ኃይል በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞዎች ከግብ እንዲደርሱ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ፈጣን ልማትን ለማስመዝገብ ግንባር ቀደም ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ተገቢ ካልሆነ ክፍፍል ራሱን በማራቅ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የተያዙ የልማት ግቦች እንዲሳኩ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል። የወጣቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት መሬት ላይ የሚታይ ተግባር ለማከናወን ከወጣቱ ጋር በየወቅቱ በመነጋገር በቅርበት እንደሚሰራ ወይዘሮ አዳነች አረጋግጠዋል። በውይይት መድረኩ ቄሮዎች/ወጣቶች/ የተፈጠረውን ችግር ተቀናጅተው ለመፍታትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ መንግስት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች እንደሚደግፉ እጅ ለእጅ በመያያዝ ቃል ገብተዋል።