ኢዜአ የህዝብ ተደራሽነት ላይ በሚፈለገው ልክ መስራት አለበት - የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የህዝብ ተደራሽነት ላይ በሚፈለገው ልክ መስራት አለበት - የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ጥር 30/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተለየ ይዘት በመቅረጽ የህዝብ ተደራሽነቱን ማስፋት እንዳለበት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተናገሩ።
ተቋሙ የህዝቡን፣ የደንበኞቹንና የመገናኛ ብዙኃንን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስራ ለማከናወን አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከመገናኛ ብዙኃን አካላት ጋር የ10 ዓመቱን መሪ እቅድ አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተወዳዳሪ የይዘት ስራዎችን ለማከናወን በሚያስችል መልኩ መገንባት እንዳለበት ተጠቁሟል።
በአደረጃጀት፣ በሰው ሃይል፣ በበጀትና በሌሎች ጉዳዮች የተሟላ ተቋም መሆን እንዳለበት ተነስቷል።
መገናኛ ብዙኃኑ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በትብብር ለመስራት የተጀመረውን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ተቋሙ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ቀላል የማይባሉ ተግባራትን መስራቱ እንደሚያስመሰግነውም ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታና ብዝሃነቷን በሚመጥን መልኩ መስራት እንደሚገባው መክረዋል።
ጋዜጠኝነት ለህዝብ በህዝብ ነውና የተቋሙ ሙያተኞች ህዝቡ የሚፈልገውን የተደራሽነት ፍላጎት ማሳካት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለደንበኞቹ ሲያበረክት ለነበረው አስተዋጽኦም የመገናኛ ብዙሃን አካላቱ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዓለም እና አገር አቀፍ ቋንቋ ተደራሽነትን በማስፋት ህብረተሰቡን ለመድረስ መስራት እንደሚገባው ተጠቁሟል።
ተቋሙ የቅርንጫፍ አማራጮች ተጠቅሞ ተደራሽነቱን በማስፋት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ለማረጋገጥ የሚስችሉ ተግባራት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ተመላክቷል።
በዜና አቀራረብ ላይ የተለየ አማራጭ ለማምጣት መስራት እንዳለበትም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስራ አመራር ቦርድ አባል ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ኢዜአ የባለድርሻ አካላትን እርካታ በማሳደግ አመኔታ የሚጣልበት ተቋም ለመሆን ግብ አስቀምጦ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ይሰራል ብለዋል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ኢዜአ የመገናኛ ብዙኃኑንና የደንበኞችን ፍላጎት ማሟላት አለብኝ በሚል የቀጣይ 10 ዓመታት እቅድ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአገር ውስጥና በአለም ዓቀፍ ቋንቋዎች ተደራሽነቱን ለማስፋት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚሰራ አስረድተዋል።