ኢትዮጵያዊነት-አብሮነት

አዲስ አበባ፣ ጥር 30/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያዊነት- አብሮነት በአብዱራህማን ናስር

የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን የሰው ልጅ በባህሪዩ ማህበራዊ ፍጡር ስለሆነ ከአብሮነት ውጪ ብቻውን መኖር አይችልም በማለት ይገልጹታል። ይህ የሰው ልጅ ማህበራዊነት ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ ያለው ስለመሆኑና አብሮነት ደግሞ የሰው ልጅ ልዩ ባህሪይ እንደሆነ ይናገራሉ። የኃይማኖት አስተማሪዎችም ይህንኑ ሃሳብ በማጠናከር ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ብቻውን እንዳይሆን ረዳት እንዳበጀለት ከቅዱሳት መጻሕፍት በማጣቀስ ሃሳቡን ያጠናክሩታል። ከዚህም ባሻገር የሰውነት አካላት በተግባርም ይሁን በዓይነት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ነገር ግን አንዱ ለሌላው እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እነዚሁ አስተማሪዎች ያብራራሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የተጻፈው “መደመር” የተሰኘው መጽሐፍ ላይ የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው ሁለት መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዳላቸው ይገልጻል። እነርሱም ቀጥተኛ ፍላጎት እና ተዘዋዋሪ ፍላጎት በሚል የተከፈሉ ሲሆኑ ሁለቱም ህልውናን የማረጋገጥ ጥቅል ፍላጎቶች መሆናቸውን ያብራራል።

ቀጥተኛ የህልውና ፍላጎት በግለሰብም ይሁን በህብረተሰብ ደረጃ የሚገለጽ የሰው ልጆች ህልውናቸውን በቀጥታ ከሚፈታተናቸው ማንኛውም የመጠቃት ስጋት ራሳቸውን የመታደግና በሕይወት የመቆየት ፍላጎት ነው። በሌላ በኩል ተዘዋዋሪ የህልውና ፍላጎቶች የስም ወይም የክብር እና የነፃነት ፍላጎቶች በሚል የተገለጹ ሲሆን እነዚህ ፍላጎቶች የማንነት ጥያቄዎችን የያዙና በራስም ሆነ በሌሎች ዘንድ ዋጋ የማግኘትና የመከበር ፍላጎቶች ስለመሆናቸው ጽሑፉ ይተነትናል። እንደ መጽሐፉ አገላለጽ  የሰው ልጆች ፍላጎቶች እርስ በርስ የተሳሰሩና ተደማሪ ፍላጎቶች ሲሆኑ በመካከላቸው ተቃርኖ ስላለ ፍላጎቶቹን በተናጠል ሳይሆን በመደመር ብቻ ሊያሳኳቸው የሚችሉ ናቸው።  

አብሮነት ለሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ሚና ያለው መርሆ ነው። አብሮነት የተለየ ማንነትን፣ ባህልን ወይም ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ በሰላም አብሮ ለመኖር መሰረት የሆነ ነው። አብሮነት የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ መቻቻል (tolerance) ከሚለው ጋር በማፈራረቅ ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) እ.አ.አ ከ1996 ጀምሮ በየዓመቱ ኖቨምበር 16 የዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን ሆኖ እንዲከበር ያስተላለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በሀገራችን ዕለቱ ሲከበር “የመቻቻል ወይም የአብሮነት ቀን” በሚል ይከበራል። ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ11ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን መሪ ቃሉም “የአብሮነት ባህላችን ለሰላማችን” የሚል ነበር።

ዩኔስኮ የአብሮነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ያደረገው የዓለም ህዝቦች በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በቀለም፣ በኃይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ልዩነቶች ምክንያት የሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ነው። በሌላ አገላለጽ በልዩነቶች ምክንያት በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብና አብሮነት ለሰው ልጆች ተሳስበው ለመኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው። የሰው ልጆች አንዱ የሌላውን ሰብዓዊ መብት በማክበርና ከሌሎች ጋር በመቻቻል መኖር ለዓለማችን ህዝቦች ወሳኝ መሆኑን ግንዛቤ ለማስረፅ ጭምር ነው። ሰዎች በተፈጥሮ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በማንነት ወዘተ የተለያዩ በመሆናቸው የሰው ልጆች አብሮ የመኖር ህልውና የሚረጋገጠው በአብሮነት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ የባህል፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የመልክአ ምድር ብዝሀነትን የተላበሰች ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ሕዝቦቿ  በአንድነት የሚቆሙበትና የሚተባበሩበት በርካታ ሀገራዊ እሴቶች አሏት። ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሟትን የውጭ ወራሪዎች ለመመከት ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ሳይለያዩ አብረው ተዋግተው ነፃነቷን አስጠብቀዋል። ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል የመተባበርና አብሮ የመፋለም እሴት ዛሬም ጎልቶ ይታያል። ለዚህም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ገበታ ለሀገር በመሳሰሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉም ዜጋ በጋራ መሳተፋቸው ጉልህ ማሳያ ነው።  

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት ገና ከመግቢያው “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች---ኢትዮጵያ ሀገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር  በመሆንዋ፣ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን እናምናለን፤” በማለት የአብሮነት እሴት የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑን በማሳየት የህገ መንግስቱ ዓላማና እምነት  አድርገው ደንግገዋል።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ትኩረት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ አመለካከት፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲሁም ሌሎች ማንነቶችን ጨምሮ ሁሉንም ያቀፈ፤ አንዱ ሌላውን ሳይደፈጥጥ ሰላማዊ ሕዝብና የበለጸገች ሀገር መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው። የሕገ-መንግስቱ መሠረታዊ ትልሙ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። በዚሁ መሰረት ህገ መንግስቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሳለፍናቸው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በርካታ ለውጦችን አይተዋል፥ የተለያዩ አዎንታዊና አሉታዊ ፋይዳ ያላቸው ትምህርቶችም ተወስደዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የህዝቦችን የሰላምና የአብሮነት ፍላጎት የማይመጥኑ፣ ትብብርና ወንድማማችነታቸውን ከማጠናከር ይልቅ የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያሻክሩ፤ በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት ከማጉላት ይልቅ ልዩነት ላይ የሚያተኩሩ፤ ከአስተዳደር ወሰንና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በአንድ በብዝሀነት ውስጥ እንዳለ ሀገር ሳይሆን በጠላትነት የሚፈላለጉ ሁለት ሀገራት እስከመምሰል የደረሱ ዘግናኝ ክስተቶች አጋጥመዋል። በተከሰቱ ግጭቶቹ የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እንዲሁም ዜጎች ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት ከተወለዱበት፣ ካደጉበት እና ለዓመታት ከኖሩበት ስፍራ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ የሚገኙት የሰላም መደፍረስ ችግሮች መንስኤያቸው በአብዛኛው ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት መሰረታዊ የህገ መንግስታዊ አስተምህሮዎች ላይ ባለመሰራቱ ነው። በእነዚህ ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የጋራ የሚያደርጋቸው እሴቶችን ከማጎልበት ይልቅ ልዩነታቸው ላይ የተሰራው ይበዛል። በተለይ በማንነት እና በሃይማኖቶች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ በር በመክፈት አንደኛው ወገን ሌላኛውን እንዲጠራጠር ብሎም በዳይና ተበዳይ እንዲመስሉ አድርጓቸዋል። በዚህ ላይ ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የአክቲቪስቶች እና የአንዳንድ ምሁራን ትርክቶች ጥላቻ እንዲነግስ እድል አግኝቷል። ይህን መሰል የአብሮነት እሴቶችን የሚሸረሽሩ አካሄዶች መታረም ካልቻሉ  የህዝቦች ዘመናት የተሻገረው አብሮነትን ከመሸርሸር አልፎ ሀገሪቱ ለማንም መሳቂያ መሳለቂያ ሊያደርጋት እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።

ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር የምትሆነው ህዝቦቿ በአብሮነት መቆም ሲችሉ ነው። እንደ ሀገር ወደኋላ መለስ ሲባል በተመጣበት መንገድ ክፍተቶች አልነበሩም ባይባልም፣ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ለነገው ትውልድ የሚሻገር ሰላም፣ አብሮነትና አንድነትን ማረጋገጥ ከዛሬው ትውልድ የሚጠበቅ ነው። በእርግጥ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን የሚሉ አካላት በሚያሰራጩት ትርክትና የተዛባ አስተሳሰብ እንጂ፣ የአገራችን ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና የአብሮነት እሴቶች ለመለያየት የማያስችሉና የተሳሰሩ መሆናቸውን ማንም የሚገነዘበው እውነታ ነው።  

የአብሮነት እሴቶች የጎለበቱባቸው ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ ሁነቶች ጠንካራ ናቸው። እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት የዓለማችን ልእለ ሃያል ያደረጋቸው አብሮነታቸው ነው። የአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች አንድ ላይ በመሆን ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በሚል ከተዋሃዱ በኋላ ነው በመላው ዓለም ተጽእኖ መፍጠር የቻሉት። ከዚህም ባሻገር ከመላው ዓለም በዲቪ እና በተለያዩ መንገዶች ሰዎችን ወደ ሀገራቸው በማስገባት ይበልጥ ሃያል ለመሆን እየሰሩ ይገኛል።

ዓለም ተነጣጥሎ ከመኖር፣ከጥላቻ፣ ቂምና ቁርሾ አትራፊ መሆን አትችልም። የሰው ልጅ ባህሪይ በመሆኑ መስተጋብር በመፍጠር በህብር መኖር ግድ ይለዋል። በሁሉም መስኮች የእርስ በርስ ግንኙነቶች፣ ልውውጦች፣ እንዲሁም ትብብርና አብሮነት የማይታዩ ከሆነ የዓለማችን መልክና ውበት መታየት አይችልም።

በኢትዮጰያ ውስጥ የተለያዩ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች እና  ልማዶች ቢኖሩም በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ የሚያመሳስላቸው ኢትዮጵያዊ ማነነት አላቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የእርስ በርስ የትብብርና የአብሮነት ታሪክ ያላቸው በመሆኑ ብዙዎቹ ማህበራዊ ግንኙነቶችና ልማዶች ተወራርሰዋል። ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ያቆዩትን እሴት ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው በአብሮነት ብቻ ነው።  አብሮነት ከሌለ ወይም ከተሸረሸረ ውስጥ ለእርስ በርስ ግጭት ከውጭ ደግሞ ለብሔራዊ ደህንነታችን ስጋት የሚሆኑ አደጋዎችን ያስከትላል። ስለሆነም ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን የአብሮነት እሴቶቻችንን ልንከባከበው ይገባል መልእክታችን ነው!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም