በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ጉርብትና - ኢዜአ አማርኛ
በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ጉርብትና

አዲስ አበባ፣ ጥር 30/2013 ( ኢዜአ) በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ጉርብትና በመንግስቱ ዘውዴ
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ልምድ ያላት ሀገር ነች። የሀገሪቱ መሪዎች በየጊዜው በሰሯቸው መልካም የውጭ ግንኙነት ሥራዎች እስከዛሬ ድረስ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ መልካም ስም እንዲኖራት አድርጓል። ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን በመመከት የአድዋ ድል ባለቤት፣ በፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሚና ያላት፣ የአፍሪካ አንድነት መስራችና መቀመጫ ሀገር በመሆኗ በዲፕሎማሲው መስክ የካበተ ተሞክሮ አዳብራለች።
ሀገራት እርስ በርሳቸው በመደጋገፍ የቆሙ በመሆናቸው የአንዳቸው ፍላጎት መሟላት በሌላኛው በጎ ፈቃድ የተመሰረተ ስለመሆኑ የተለያዩ ጽሑፎች ያመለክታሉ። መደመር በተሰኘው መጽሐፍ ስለውጭ ግንኙነት ሲተነትን በሀገራት መካከል የሚኖር ግንኙነት በመቀናቀንና በመጠላለፍ ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይገባውም። ይልቁንም በትብብርና በጋራ በመሥራት በመካከላቸው መተማመንን እንዲሰፍን ያደርጋል በማለት ያብራራል። ከዚሁ ጋር በማያያዝ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እሳቤ ጥቅምን ሳይሆን ግንኙነትን ያስቀደመና ችግሮችን ለመፍታት ቀዳሚው ነገር ግንኙነትን ማደስ መሆኑን ያሰምርበታል።
በተሻሻለው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረው ዲፕሎማሲ የመጀመሪያ ትኩረቱ በመተባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠርና ማጠናከር ነው። ፖሊሲው ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ዘመናትን ያስቆጠረ በመሆኑ እነዚህን ግንኙነቶች ይበልጥ በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ላይ ትኩረት አድርጓል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት ሀገራት እኩል ዕይታና ቀረቤታ እንዲሁም መልካም ግንኙነት እንዳላት በማሳያነት ከሚቀርቡ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የጎረቤት ሀገራት ዜጎችን በስደተኝነት ተቀብላ በዓለም አቀፍ የስደተኞች አያያዝ መርህ መሰረት ማስተናገዷ ነው፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ከኤርትራ፣ ከየመን፣ ከሶሪያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን እንዲሁም ከሶማሌ ተሰደው የገቡ እና አሁንም ጭምር በኢትዮጵያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ያሉትን ማየት በቂ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟ ሊረጋገጥ የሚችለው በጎረቤት ሀገራት ያለው መረጋጋት ዘላቂ መሆን ሲችል እንደሆነ በጽኑ ታምናለች፡፡ ለዚህም ነው በማናቸውም ወቅቶች በጎረቤት ሀገራት የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የራሷን ሚና ስትጫወት የቆየችው፡፡ ለዚህም በቅርቡ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በሀገሪቱ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲመጣ ለማድረግ በወታደራዊው ሀይልና በሲቪሉ መካከል ሰላማዊ ድርድር እንዲደረግ ድጋፍ ያደረገችው እንደማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሀይል ስር በመሆን በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ በመሰማራት በሀገራቱ ሰላም እንዲሰፍን ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ይመሰክራል። ከዚህ በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት የሚያስችሉ እንደ የባቡር መስመር፣ የየብስና የአየር ትራንስፖርት ዝርጋታ፣ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦ፣ የቴሌኮም ኔትዎርክ ዝርጋታና የሀይል መስመር ግንኙነት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ የወደብ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመቀናጀት እየሰራች ትገኛለች። ለሀገራቱ ጠንካራ ግንኙነት መመስረት የህዝቦች የጋራ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ማህበራዊ እሴቶችና ቋንቋ፣ ታላቁ የአባይ ወንዝ፣ የባሮ ወንዝና የሚጋሩት የጋራ ድንበር ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በተዘዋዋሪ ሀገራቱ በአንድ ወንዝ የተጋመዱ ህዝቦቹም የአንድ ምንጭ ውሃ ጠጪዎች መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት የሆኑት ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ከሀገራችን ጋር የሚጋሩት የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የመሳሰሉት ግንኙነቶች አላቸው። በመሆኑም በሀገራችን የሚከናወኑ ሁነቶች በቀጥታ ጎረቤት ሀገራትን የሚነካ እንዲሁም በጎረቤት ሀገራት የሚከወኑ ሁነቶች ሀገራችንን በቀጥታ የሚመለከት ይሆናል ማለት ነው። ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተለያየ መልኩ የሚገለጹ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮች መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም ግንኙነት በማንኛውም መልኩ የተሳሰረ በመሆኑ የጋራ ጥቅሞችን ያማከለ ትብብር እንደሚያስፈልግ እሙን ነው።
ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር በድንበር የምትዋሰን ሲሆን በፖለቲካዊና ማህበረ-ኢኮኖሚው ዘርፍ ረጅም ጊዜ የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪክ አላት። በተለይ በወደብ አገልግሎት እና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት ማሳያዎች ናቸው። ከኬንያም ጋር እጅግ መልካም የሚባልና በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው፡፡ ሁለቱ ሀገራት አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ በመከባበር ኖረዋል። በተመሳሳይ ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ጋርም ለብዙ ዘመናት የቆየ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ከመሆኑም በላይ በሁለቱ ሀገሮች ተሰባጥረው የሚኖሩ ህዝቦች መኖራቸውን የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት መነሻውን የሚያደርገው እኤአ በ1896 ላይ መሆኑን ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ የንግድ መስመር ሱዳንን፣ ግብጽንና ሜዲትራኒያን ባህርን አልፎ ይሄድ እንደነበርና ከሱዳንም የሙስሊም ነጋዴ ባለሃብቶች በሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ ይሁንና ሁለቱ ሀገራት መደበኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት ሱዳን ነጻ ሀገር ሆና ከተመሰረተችበት እኤአ ከ1956 ጀምሮ ነው፡፡
የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት ልክ ከሌሎች ሀገራት ጋር እንዳለው በህግ ከተደነገገ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ከሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ የደም ትስስር፣ ወንድማማችነት፣ የጋራ መተማመንና እርግጠኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል አሁንም ይኸው የህዝቦች ግንኙነት እንዳይበላሽ ያላትን ጽኑ ፍላጎት በተደጋጋሚ እየገለጸች ትገኛለች።
ኢትዮጵያና ሱዳን ከ1600 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ድንበር ይዋሰናሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በድርድርና በውይይት መፍታት የሚያስችላቸውን ስምምነት እኤአ በ2007 ተፈራርመዋል፡፡ ይህ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኘው የድንበር ማካለል ጉዳይ ለዘመናት የችግር ምንጭ ሳይሆን የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በሱዳን በኩል “ግዛቴ ነው” የሚል ወጣ ያለ አቋም በመያዝ የሁለቱ ሀገራት የቆየ ግንኙነት እንዲሻክር መንስኤ መሆኗን በግልጽ እየታየ ነው።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ በነበረችበት ወቅት የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸው የሁለቱን ሀገራት ህዝቦችና መንግስታት ታሪካዊ ግንኙነት የማይገልጽ በመሆኑና ቀጣዩን የሀገራቱን ግንኙነት ማበላሸት ስለማይገባ ሱዳን ጦሯን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል አሁንም እያቀረበ ይገኛል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት እኤአ በ1972 የሀሳብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመው ድንበራቸውን እንደገና ለማካለል መስማማታቸውን በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድንበር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ቴክኒካል አማካሪና በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባል የሆኑት አቶ ውሂብ ሙሉነህ ያስረዳሉ። ስምምነቱ በተባበሩት መንግሥታት የተመዘገበ መሆኑን በማንሳት ሁለቱ ሀገራት የሚቀበሉት የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የድንበር ነባራዊ ሁኔታው ባለበት ተከብሮ እንዲቆይ መስማማታቸውንም አክለው ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያና የሱዳን ህዝቦች በማህበራዊም ይሁን በስነልቦናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሳሰሩ ናቸው። እናም ከጦርነት ይልቅ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ መከተል ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ሰላምና መረጋጋት ብሎም ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶች ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በውይይትና በድርድር እንዲሁም በነባር የሁለትዮሽ መድረኮች በሰላማዊና ዘላቂ ጥቅማቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ መፍታት አዋጭና የሰለጠነ አካሄድ ነው። ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚደረጉ የረዥም ጊዜ መልካም ግንኙነቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የጋራ ጥቅምን በሚያስከብር መርህ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ መስራት የሁሉም ጎረቤት ሀገራት ድርሻ ሊሆን ይገባል። ከጎረቤት ሀገሮች ጋር አብሮ መስራት ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ በመረዳት በሚያጋጥሙ የጋራ ችግሮች፣ ስጋቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ በጋራ መስራት ከሀገራቱ የሚጠበቅ ነው።