ቀጥታ፡

ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መቐለ ገቡ

መቐለ ፣ ጥር 30/2013 ( ኢዜአ) የኢፌዲሪ ፕሬፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዛሬ መቐለ ከተማ ገብተዋል።

ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በመቐለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕሬዚዳንቷ በመቐለ ከተማ የሚገኘውን አይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በከተማዋ የሚገኘውን የፌደራል መንግስት ማዕከላዊ መጋዘን ጎብኝተዋል።

በማዕከላዊ መጋዘኑ ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል ለሁለት ወር የሚበቃ የእህል ክምችት መኖሩም ተገልጿል።

ፕሬዝዳንቷ በመቀሌ ቆይታቸው ከሐይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋርም ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በትናንትናው ዕለት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚልና የአለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ አሰጣጥ ያለበትን ሁኔታ መጎብኘታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም