ቀጥታ፡

በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳካት እየተሰራ ነው

ባህርዳር ጥር 29/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የቀየሰችውን በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳካት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዴሪ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ከአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና ዱር እነስሳት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

የኢፌዴሪ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር  ፈቃዱ  በየነ  በግምገማው መድረኩ እንዳሉት  መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ  የሚያስከትለውን  ቀውስ ለመቋቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎቸ በማካተት እየተሰራ ይገኛል።

ለዚህም የአካባቢ ጥበቃ፣ ደን ልማት፣ ዱር  እንስሳት ደህንነት  ማረጋገጥና ሌሎች  ተያያዥ  ተግባራት ላይ በህዝብ ተሰትፉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች የሚተከሉበት  የአረንጓዴ አሻራ  መርሃ ግብርና  በየአካባቢው የሚካሄደው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በማሳየነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በከተሞች የሚስተዋለውን የፍሳሽና የተደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ በማሻሻልና በኢንዱስትሪዎች ላይ የሚካሄደው የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማን በማጠናከር ለነዋሪዎችና ለጎብኞች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ትኩር መሰጠቱን አስረድተዋል።

በባህር ዳሩ መድረክ  በክልሎች የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን  ለማሳየትና  ቀጣይ  አቅጣጫዎች ላይ መግባባት በመፍጠር በቅንጅት ለመሰለፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል የአከባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቀና ልማት ባለስልጣን ዋና  ዳይሬክተር  ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው በአካባቢ ጥበቃ የሚካሄደው የልማት ተግባራት የዱር እንስሳትን ደህንነት ለማረጋገጥ መሰረት ነው ብለዋል።

ከደን ጥበቃና ዱር እንስሳት ጋር ተያይዞ ዘላቂ ልማት ለማካሄድ የሚያስችል የልየታ፣ የመሰረተ ልማት ማሟላትና እንክብካቤ በማካሄድ የየአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እስከ ቀበሌ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች በግንዛቤ ፈጠራ፣ አካባቢዎችን በመጠበቅና በመንከባከብና ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

የባለስልጣኑ የእቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ አበጀ ገነቱ እንደገለጹት በክልሉ ዘጠኝ የአረንጓዴ ልማት የሚካሄድባቸው ጥብቅ ስፍራዎች ተለይተው ወደ ስራ ተገብቷል።

በችግኝ ማፍላት፣ በደን ዘር አቅርቦትና በሌሎችም የዘርፉ ልማት  ላይ ከ72ሺህ በላይ  የህብረተሰብ  ክፍሎች የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል።

በደን ልማቱ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱም የአካባቢ ድህንነትን ለማሳደግና የዱር እንስሳትን ደህንነት በማስጠበቅ ለቱሪዝም ለማዋል እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ባለስልጣን አቶ ሽታዬ ዩሙራ በክልሉ ከቡና እጥበትጋር ተያይዞ የሚከሰት የወንዞች ብክለትን ለማስወገድ በግማሽ ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን  አብራርተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ሀገር አቀፍ መድረክም ከሁሉም ክልሎች፣ የአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም