ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የመጠጥ ውሃ አግኝቷል

ጥር 29/2013 (ኢዜአ) በኢተዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማግኘቱን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ባለፉት ስድስት ወራት ሚኒስቴሩ በስሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት አብራርተዋል።

በግማሽ ዓመቱ በፌዴራል በተያዙ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ከ219 ሺህ በላይ እንዲሁም በክልሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተጠቃሚ ሆኗል።

በአጠቃላይ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

ሚኒስትሩ በተመሳሳይ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ ከተከናወኑ ሥራዎች በተጓዳኝ 142 ሺህ ደምበኞች ኃይል እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት አንድ ሚሊዮን አዳዲስ ደምበኞች ሃይል እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የጂኦ-ተርማልና የፀሐይ ኃይል ያሉ አማራጮችና 15 ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያና ማሰራጫ ጣቢያዎች ግንባታ እየተከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ከደምበኞቹ 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ታሪፍ መሰብሰቡንም ተናግረዋል።

ካገለገሉ መሳሪያዎች ሽያጭና ከኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ሰባት ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም አክለዋል።

የበጋ መስኖን በመጠቀም የቆላ ስንዴ ለማምረት እየተሰራ ሲሆን፣ መስኖን ለማስፋፋት ከ5 ሺህ በላይ ፓምፖች መከፋፈላቸውም በግማሽ ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ጠቅሰዋል።

በነባር መስኖ ፕሮጀክቶች ስንዴ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ኢንጂነር ስለሺ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከውጭ ስንዴ ለማስገባት በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርግ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም