ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ ''የዳር ተመልካች'' መሆን የለባቸውም - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ ''የዳር ተመልካች'' መሆን የለባቸውም
ጥር 29/2013 (ኢዜአ) ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ ''የዳር ተመልካች'' ከመሆን በ'ያገባኛል' ስሜት ሙያዊ አበርክቷቸውን ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመለከተ።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ብሔራዊ ጥቅሟና ደህንነቷ የተረጋገጠ አገር በመገንባት ሂደት የምሁራን ሚና" በሚል ርዕስ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
በመድረኩ "ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነትና ጥቅምን ለማስከበር በታሪክ ያደረገቻቸው ተጋድሎዎች በትውልድ ቅብብሎሽ የዜጎች ኃላፊነት"፣ "የአገር በቀል እውቀቶችና ልምዶች ውስጣዊ ችግሮቻችንን ከመፍታት አንጻር የባህል ተቋማት ሚና" እንዲሁም "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድባችን አንድነታችንና ሉዓላዊነታችንን ከማስከበር አንጻር ያለው ሚናና የዜጎች ተሳትፎ" በሚሉ ርዕሶች የመነሻ ጽሁፎች ቀርበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለሠላም፣ ለአብሮነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሐሳብ ልዕልና የሚያምን ትውልድ መፍጠር ይገባል።
ምሁራን ሐሳቦችን በማፍለቅ ትውልድ እንዲማርበትና እንዲመራበት በማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ምሁራን ከዝምታ በመውጣት በአገር ጉዳይ ላይ በሐሳብ በመሞገትና ገንቢ አስተሳሰቦችን ማፍለቅ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ /ኢዜማ/ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ አበበ አካሉ አገር ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከትና ድርጅት በላይ በመሆኗ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንዲቆይ አስተዋጽኦ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዚህም ምሁራን የሐሳብ መድረኩን በመያዝ ብሔራዊ ደህንነቷና ጥቅሟ እንዲከበር አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ደግሞ ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ በምን ዓይነት መልኩ አስተዋጽኦ ያድርጉ? ከሚለው ሐሳብ በፊት መምጣት ያለበት ምሁራን በጎራ ከተከፋፈሉባቸው ሐሳቦች ወጥተው ድምጻቸውን እንዴት ማሰማት አለባቸው? የሚለው ጉዳይ ሊተኮርበት አንደሚገባ ተናግረዋል።
ምሁራን ለአገር ልማትና እድገት ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረግ 'ይጠበቅብናል' ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በሚመለከት የኢትዮጵያን አቋም በዓለም አቀፍ መድረኮች በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገብረመስቀል ጠና የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ምሁራን ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሐሳብ ልዩነቶችን ወደ ጎን በማድረግ ኢትዮጵያ ያሉባትን ችግሮች በመተንተንና መፍትሔዎችን በማመላከት የተጋረጡባትን ፈተናዎች እንድትሻገር መስራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር አልማው ክፍሌ በበኩላቸው በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሰሩ ምሁራን በአገር ጉዳይ "ከዳር ተመልካችነት" መውጣት ይገባናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያም ፈተናዎቿን ለማለፍ የምሁራንን ሙያዊ አስተዋጽኦ እንደምትሻ አመልክተው፤ አገራዊ ተሳትፏቸውን በማጠናከር ትውልድ የማነጽ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ሚኒስቴሩ ምሁራን በአገር ጉዳይ ሙያዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ቋሚ የምክክርና ሃሳብ ማቅረቢያ መድረክ እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
መድረኩ ከምሁራን በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚያካትትም ጠቁመዋል።
ምሁራን አገራቸው የተጋረጡባትን ፈተናዎች አልፋ የብልጽግና ማማ ላይ እንድትወጣ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ዶክተር ሳሙኤል አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳትና በመሞገት አስተዋጽኦ እያደረገ ለሚገኘው መሐመድ አል አሩሲ የዋንጫ ሽልማት አበርክቷል።