የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደምበኞቹ በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦች ሊያቀርብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደምበኞቹ በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦች ሊያቀርብ ነው
ጥር 29/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦችን ለደምበኞቹ ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
አየር መንገዱ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ምግቦች የሚያስተዋውቅበት ዘመቻ እንደሚጀምርም ገልጿል።
ዘመቻው "ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ይብረሩ፣ ተፈጥሯዊ ማዕድ ይቋደሱ" በሚል ሃሳብ ይካሄዳል ብሏል።
ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ከጤፍ፣ ከኑግ፣ ከሥጋ፣ ከቆጮ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚዘጋጁ ምግቦችና ለጤና ተስማሚ መጠጦች በሚያቀርባቸው ማዕዶች ተካተዋል።
ምግቦቹ ብቃታቸው ከተረጋገጠ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር በትስስር የሚቀርቡ ሲሆን፤ የተፈጥሮ ይዘታቸውም አስተማማኝ እንደሆነ ተመልክቷል።
በዘመቻው ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ መንገድ የምታመርታቸውን የግብርና ምርቶች ለተጓዦች በማስተዋወቅ በዓለም ገበያ ያላቸውን ተፈላጊነት ለመጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።
በአየር መንገዱ የበረራ ምግብ ዝግጅት ክፍል ኃላፊ አቶ በላይነህ አስፋው እንዳሉት የተፈጥሮ ምግቦችና ኢትዮጵያዊ ጣዕምን በሚያስተዋውቅ መልኩ ለደምበኞች ለማቅረብ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ለዚህም ምርቱ ከሚመረትበት ሂደት ጀምሮ የስነ-ምግብ ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያዊያን የምግብ ባለሙያዎችና ሌሎችን በማሳተፍ ደምበኞች በሚወዱት መልኩ ይቀርባል ብለዋል።
ዘመቻውን ለማካሄድ ለታዋቂ የምግብ ባለሙያዎች፣ ለተጓዦችና ሌሎች በማቅመስ አዎንታዊ ግብረ መልስ መሰብሰቡን አውስተዋል።
የስነ- ምግብ ባለሙያው አቶ አብነት ተክሌ አየር መንገዱ ኢትዮጵያዊ ጣዕምን የሚያስተዋውቁ በተፈጥሮ ይዘታቸው የሚለዩ ምግቦችን በማቅረቡ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ለደምበኞች የሚቀርቡት ምግቦች የንጥረ ነገር ይዘታቸው መረጋገጡን አብራርተዋል።
አየር መንገዱ ምግቦቹን ለደምበኞቹ ከማቅረብ ባለፈ የግብርና ምርት አቅራቢዎችና አምራቾች ምርታቸውን ለአውሮፓ፣ ለአሜሪካና ለመካከለኛው ምስራቅ ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
የግብርና ምርቶች አቅራቢዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያን ምግብ በማስተዋወቅ ለዓለም ገበያ ተደራሽ የማድረግ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
ምግቦቹ በሰው ሰራሽ ማዳበሪያ፣ በዘረመል ማሻሻያና በሌሎች ሰው ሰራሽ ንጥረ ነገሮች የተመረቱ መሆናቸው በደምበኞች ተመራጭና ተወዳጅ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አየር መንገዱ ዶሮ ወጥን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ጣዕም ያላቸውን ምግቦች ለደንበኞች እያቀረበ ነው።
የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በሚገኙበት የዘመቻው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ይካሄዳል።
በቀጣይም በዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የማስተዋወቂያ መርሐ ግብሩ ይቀጥላል።
አየር መንገዱ በዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለምግብና መጠጥ ግዥ የሚያወጣ ሲሆን፤ ከአገር ውስጥ የሚገዛው10 በመቶውን ብቻ ነው።
ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውንና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦችን ማቅረብ ሲጀምር የአገር ውስጥ ግዢውን ወደ 25 በመቶ ለማድረስ አቅዷል።