የአደዋ ተጓዦች በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የምግብ እህል ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የአደዋ ተጓዦች በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የምግብ እህል ለገሱ
ደሴ፤ ጥር 29/2013 (ኢዜአ) ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡ የአደዋ ተጓዦች በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከሁለት ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል መለገሳቸውን የተጓዦቹ ዋና አስተባባሪ ወጣት ያሬድ ሹመቴ ገለጸ፡፡
አስተባባሪው ለኢዜአ እንዳለው የጉዞ አደዋ ተሳታፊዎች ድጋፉ ያደረጉት በሚያልፉባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማስተባበር ያሰባሰቡትን ነው።
ከለገሱት መካከል የዳቦ ዱቄት፤ ማኮረኒ፤ ሩዝና ፓስታ እንደሚገኙበት ጠቁሞ ከዚህ ድጋፍ ግማሹ መቀሌ መድረሱንና ቀሪውን ደግሞ ከፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር ተቀናጅተን በማጓጓዝ ላይ ነን ብሏል፡፡
ችግሩን ለማለፍ ሁላችንም መተጋገዝ ይኖርብናል ያለው ወጣቱ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግም ከተለያዩ ድርጅቶችና በጎ ፍቃደኞች ጋር እየሰራን መሆኑን ተናግራል፡፡
አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከሚመራው ግሎባል አሊያንስ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበርም ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ለማካሄድ ቅደመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ጠቁሟል፡፡
ለድጋፉ የሚሆን ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ዛሬና ነገ በጣይቱ ሆቴል አዲስ አበባ ተጀምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞችም ይቀጥላል ብሏል፡፡
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ዘመቻ ከ42 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ጥሬ ገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመሰብሰብ መታቀዱንም ወጣት ያሬድ አስታውቋል፡፡
ድጋፉ በትግራይ እና ቤኒሻንጉል መተከል ዞን ለተፈናቅሉ ዜጎች የሚሰጥ ነው ብሏል፡፡
በተለያዩ ጊዜ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ጥሩ ምላሽ እንደጣቸው ጠቁሞ እቅዳችን እንዲሳካ ህዝቡ በተለመደው ትብብሩ ወገኖቹን እንዲደግፍ መልዕክቱን አስተላልፋል፡፡
የጉዞ አደዋ ሌላው አስተባባሪ ወጣት ደረጀ ገብረ ዜና በበኩሉ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ለመደገፍ ባደረጉት እንቅስቃሴ የህብረተሰቡ ድጋፍ የሚደነቅ ነው ብሏል፡፡
ወጣቱ እንዳለው የአደዋ ጉዟቸው እየተሸረሸረ የመጣውን የኢትዮጵያ አንድነትና ፍቅር የአደዋ ድልን በመዘከር ለመመለስ እንደ መሸጋገሪያ ድልድ ለመሆን ነው።
የአደዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት ጭምር በመሆኑ በተለያዩ ሀገራትም እንዲከበር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጾ አፍሪካዊያንን ለማስተሳሰር ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብሏል፡፡
የአደዋ ተጓዦች ከተቋቋሙበት ዓላማ በተጨማሪ የተቸገሩ ዜጎችን ለማገዝ የሚያርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ ባህል ፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው ናቸው፡፡
የኢትዮጵያውያን የአንድነት፤ አብሮነትና የመተጋገዝ ልምድ ለትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ጠቁመው ህብረተሰቡ ሊደግፋቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብራቸውም እንዲሳካ ደሴ ከተማ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ስምንተኛው ዙር የአደዋ ተጓዦች በደሴ ከተማ ለሁለት ቀናት በመቆየት በአካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን መገብኘታቸውንና ትናንት ወደ ሐይቅ ከተማ ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡
ተጓዦች በቀን እስከ 40 ኪሎ ሜትር መንገድ በእግራቸው በመሄድ 125ኛውን የአደዋ የድል በዓል በቦታው ያከብራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡