የመንጃ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ለማግኘት እንግልት እየደረሰብን ነው - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመንጃ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ለማግኘት እንግልት እየደረሰብን ነው - ተገልጋዮች

ጥር 29/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የመንጃ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ለማግኘት ለተደጋጋሚ ምልልስና እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።
የከተማዋ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ የመንጃ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ክፍተቱ በግብዓት እጥረት የተከሰተ ነው ብሏል።
ኢዜአ በመዲናዋ የመንጃ ፍቃድ እድሳት አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ክፍለ ከተሞች በአራቱ ላይ ቅኝት ያደረገ ሲሆን ተገልጋዮችም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን ገልፀውለታል።
በቦሌ፣ በቂርቆስ፣ በየካ እና ላፍቶ ክፍለ ከተሞች አገልግሎት ፈልገው የመጡ ባለጉዳዮች በተደጋጋሚ የሚመላለሱት ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ ለመቀበል እንደሆነ ነው የገለጹት።
በተለይ ከመንጃ ፈቃድ እድሳት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጊዜያዊ መንጃ ፈቃድ እንድንወስድ ተደርገናል ያሉት ተገልጋዮቹ፣ በየጊዜው ወደ ተቋሙ በመመላለስ ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
የተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ ፍጥነት የጎደለው መሆኑ የስራ ሠዓታቸውን እያባከነባቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
አገልግሎት ለማግኘት ረዥም ሰልፍ መጠበቁ ለኮሮና ቫይረስ ጭምር የሚያጋልጥ መሆኑን የጠቆሙት ተገልጋዮቹ ዳተኝነትን በማስቀረት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ አመልክተዋል።
በክፍለ ከተሞቹ የባለስልጣኑ ቅርጫፎች የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለቅሬታው ምክንያቱ ለመንጃ ፈቃድ መስሪያ ግብዓቶችና መሳሪያዎች እጥረት ነው ይላሉ።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ አገራት በራቸውን ዝግ በማድረጋቸው ግብዓቶቹን ከውጭ አገር ለማስገባት እንቅፋት በመሆኑ ጊዜያዊ መንጃ ፍቃድ ለመስጠት መገደዳቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የቦሌ ክፍለ ከተማ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ታዬ እና የባለስልጣኑ የንፋስስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው ለማ፡-
ኢዜአ የቅርጫፍ ኃላፊዎቹን ምላሽ በመያዝ የአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ችግሩን ለመፍታት ምን እየሰራ ነው? ሲል ጠይቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አደም ኑር ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ይላሉ።
25 የመንጃ ፈቃድ ማተሚያ ማሽኖች ግዥ ለመፈጸም የ5 ሚሊዮን ብር ውል መገባቱንና በጊዜያዊነትም ያሉትን ማሽኖች በመጠገን ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ስለሚያደርጉት ጥንቃቄ ድንገተኛ የመስክ ምልከታ የሚያደርገው ጤና ሚኒስቴር በአብዛኞቹ ክፍተቶች እንደሚታዩ ይገለጻል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ የጥንቃቄ ጉድለቶችን በቦታው በመገኘት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል ብለዋል።