በመቀሌ ማረሚያ ቤት ውስጥ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት አደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ ማረሚያ ቤት ውስጥ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ጉዳት አደረሰ
መቀሌ ሀምሌ18/2010 በመቀሌ ማረሚያ ቤት ውስጥ ዛሬ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ማረሚያ ቤቱ አስታወቀ፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ይትባረክ አለነ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ቃጠሎው በታራሚዎች የተለኮሰ እሳት ነው ተብሎ ተጠርጥሯል፡፡ ዛሬ ስምንት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ከሁለት ሰዓት በላይ የቆየው የእሳት ቃጠሎው ባደረሰው አደጋ የአንድ ታራሚ ህይወት ሲያልፍ በሌሎች 12 ታራሚዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ለጊዜው ግምቱ ባልታወቀ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ያመለከቱት ኃላፊው በከባድ የተጎዱት ታራሚዎችም ለተጨማሪ የህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የእሳት ቃጠሎው በመቀሌ ከተማ የእሳት ማጥፊያ ብርጌድ፣በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የእሳት ማጥፊያ ቡድን አባላት፣ የማረሚያ ቤቱና የፖሊስ ልዩ ኃይል ትብብር መቆጣጠር መቻሉም ተመልክቷል፡፡