ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አንድነታችንን ያረጋገጥንበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ... የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አንድነታችንን ያረጋገጥንበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ... የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

ሐረር ፤ጥር 29/2013(ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያውንን አንድነት እና የይቻላል መንፈስን ያረጋገጥንበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ሐረሪ ክልል በገባበት ወቅት የተገኙት ወይዘሮ ሚስራ አብደላ "እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ስንሆን ካሰብንበት ቦታ መድረስ እንችላለን" ብለዋል።
"የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን በተግባር ያረጋገጥንበት ነው፤ ለመጪው ትውልድ የይቻላል መንፈስን ያሰረፅንበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ከወዲሁ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያውያን ፍሬያቸውን ለማየት የተቃረቡበት መሆኑን አስረድተዋል።

ከግድቡ ጋር ተያይዞ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የተጀመረውን ድርድር ለማሳካት ኢትዮጵያን ወክለው በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላትን ምክትል ርዕሰ መስተደድሯ አመስግነዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እንዲዳብር እና የህዝቦችን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ለማሳየት እድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ዋንጫው በክልሉ በሚቆይባቸው ሁለት ወራት በዘጠኙም ወረዳዎች ተዘዋውሮ በየደረጃው የሚገኝ የክልሉ ነዋሪ እንዲሳተፍ ይሰራል በማለት፤ የክልሉ ህዝብም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ እንደከዚህ ቀደሙ ድጋፋን እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፈዋል።
"የብልጽግና ጉዟችን መሸጋገሪያ የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለማሰናከል የሚያደረጉ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች አንታገስም" ሲሉ ገልጸዋል።
በዋንጫው አቀባበል ሥነ-ሥርዓት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ አዲስ አለም በዛብህን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።