ኢዜአ በዓለም አቀፍ ዜና አገልግሎቶች ተወዳዳሪ በሚሆንበት ልክ መስራት ይጠበቅበታል- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በዓለም አቀፍ ዜና አገልግሎቶች ተወዳዳሪ በሚሆንበት ልክ መስራት ይጠበቅበታል- የፖለቲካ ፓርቲዎች
ጥር 29/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከዓለም አቀፍ ዜና አገልግሎቶች ጋር ተወዳዳሪ በሚሆንበት ልክ መስራት እንደሚጠበቅበት የፖለቲካ ፓርቲዎቸ ተናገሩ።
ተቋሙ በ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታው ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ፓርቲዎች ዓላማቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህብረተሰቡ የሚያስተዋውቁበት እንዲሁም በአጋርነትና በትብብር የተዘጋጁ የይዘት ስራዎችን የሚያገኙበት ሥርዓት እንደተዘረጋ ተገልጿል።
ፓርቲዎቹ ተቋሙን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማዘመን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴና በፍኖተ- ካርታው የተቀመጡ እሴቶች በጎ ጅምር መሆናቸውን ገልፀዋል።
ኢዜአ ራሱን ከዓለም አቀፍ ዜና አገልግሎቶች ጋር በማወዳደር ራሱን ከፍ ወደዳለ ስፍራ ማድረስ አንዳለበት ገልጸዋል።
ኢዜአ ፈጣንና ትክክለኛ ዜናዎችን ለህዝብ በማድረስ በገበያው ተፎካካሪና ተወዳዳሪ መሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥላሁን ጀልሶ ኢዜአ ሰፊ የህዝብ መሰረት ያለው፣ በአሰራሩ ነፃና ትክክለኛ መረጃ እንዲያሰራጭ በአዲስ መልክ መቋቋሙን ገልጸዋል።
ተቋሙ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ያቀዳቸውን ሥራዎች አቅሙን በማጎልበትና አሳታፊ በሆነ መንገድ በመተግበር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ከጎረቤት አገሮች ጋር ትስስር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተያዙ ነጥቦች መልካም መሆናቸውን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
እውነተኛ መረጃ ቀድሞ በመስጠት አሉታዊ ዘገባዎችን ለማስተካከል የተሄደበትን መንገድም አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ከተሳታፊዎቹ የተነሱ ሃሳቦች በዕቅዶቹ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚያግዙ ገልጸዋል።
ዕቅዱ ሲዘጋጅ አገሪቱ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የምትደርስበትን ደረጃ በመገምገም ትንታኔ እንደተሰራበት አመልክተዋል።
ተቋሙ ከፓርቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።
ተቋሙ ቀደም ሲል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተመሳሳይ መድረክ ማካሄዱ ይታወሳል።
ኢዜአ 79 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋና ብቸኛ የኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት ተቋም ነው።