በሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም
ጥር 28/2013 (ኢዜአ) በሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ወደ ስምምነት እንዳይደረስ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለውና ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ድርድሩ እስካሁን ያለፈባቸውን ሂደቶች ዘርዝረው በቀጣይ በሚኖሩ ሁኔዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ አጠቃቀም ትብብርን፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና መልካም ጉርብትናን ማዕከል በማድረግ እሳቤ ይዛ እየሰራች ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ በቅኝ ገዥዎች እሳቤ የተቃኘውን "በግብጽና በሱዳን በኩል ያለው ችግር ኢትዮጵያ እንኳን አመንጭዋ አገር የማትለውን እኛ ብቻ እንጠቀም እናንተ በድህነት ቆዩ" የሚለው እሳቤ ክርክር ውስጥ ያስገባ መሆኑን አብራርተዋል።
እስካሁን በተካሄዱ ሰባት ስብሰባዎች ግብጽና ሱዳን በየጊዜው ተለዋዋጭ አቋም ይዘው መምጣታቸው ስምምነት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ አድርጎታል ነው ያሉት።
የሁለቱ አገራት አካሄድ "በህዳሴ ግድብ ድርድር በማስታከክ አብረን ፈርመናል የሚሉትን ውል ኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ነው" ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ 1959 ስምምነት የሚያስገቡ ጉዳዮች ተቀባይነት የላቸውም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ ፍላጎት የውሃ ክፍፍል ባለመሆኑ ለሚፈረሙ መመሪያዎች ተገዥ በመሆን የውሃ ሙሌቱ ጉልህ ጉዳት እንዳያስከትል በስምምነቱ በሰረት በጥንቃቄ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከአገራቱ የሚመጡ ጊዜ የሚፈጁና ወደ ስምምነት እንዳይደረስ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረጉ ሙከራዎች እንደ ሉዓላዊ አገር ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።
ከግብጽና ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሕዳሴ ግድብ ጋር የማይገናኙ ማዕቀፎችን የማምጣት አካሄድ እንደሚስተዋልም አብራርተዋል።
የመጨረሻው የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር የተካሄደው ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።