ክልሎች የገቢ አቅማቸውን በመለየት የታክስ አሰባሰባቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል ... አፈ-ጉባዔ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎች የገቢ አቅማቸውን በመለየት የታክስ አሰባሰባቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል ... አፈ-ጉባዔ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2013(ኢዜአ) ክልሎች የገቢ አቅማቸውን በመለየት የታክስ አሰባሰባቸውን ማሳደግና ማጎልበት እንደሚኖርባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ አስገነዘቡ።
ምክር ቤቱ በፌዴራል የመሰረተ ልማት ተቋማት የስርጭት ዝግጅት፣ በጋራ ገቢ አስተዳደርና ማከፋፈያ ቀመር አፈጻጸም ላይ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድር፣ ከፌዴራልና ከክልል የስራ ሃላፊዎች ጋር መክሯል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የመስኖ ልማት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና የኢንዳስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ተሳትፈዋል።
በተቋማቱ ለክልሎች በሚያደርጉት የሃብት አከፋፈል ቀመር ላይ የተዘጋጁ የእቅድ አፈጻጸም ሰነዶች ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በዚሀም የአገሪቷ አጠቃላይ የመሰረተ ልማት ፍትሃዊ ተደራሽነት ጥያቄ ሲነሳበት እንደነበር ተመላክቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለክልሎች ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት በምሳሌነት ተጠቅሷል።
የአገሪቷን የኤሌክትሪክ ሽፋን በ2025 ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑም በቀረበው የመነሻ እቅድ ተገልጿል።
አፈ-ጉባዔ አደም ዜጎች የኑሮ ሁኔታቸውን የማሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማስመዝገብ ህገ-መንግስታዊ መብት እንዳላቸው አንስተው መንግስትም ፍትሃዊ የሃብት ስርጭት እንዲኖር የመከታተል ግዴታ አለበት ብለዋል።
በፌዴራልና በክልል መንግስታት የሚከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የመሰረተ ልማት ስራዎች በህገ-መንግስቱ መርህ እየተመሩ የዜጎችን እኩል የመልማት ፍላጎት ማረጋገጥ አለባቸውም ብለዋል።
በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ሠላምና ዋስትና ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት በመዘርጋት ልማትን ማረጋገጥ ደግሞ ህገ-መንግስታዊ መርህን ተግባራዊ የማድረግ ዋነኛ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የዜጎችን ቀጣይነት ያለው ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም አፈ-ጉባዔው አመልክተዋል።
ለመሰረተ ልማት ስርጭት ተጠቃሚነት የተመረጡ የፌዴራል ተቋማት ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጡ መስፈርቶች አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ መደረጉ ዋነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
የተሰበሰበው የጋራ ገቢም በምክር ቤቱ በተወሰነው የክፍፍል ቀመር መሰረት በትክክልና በወቅቱ መተላለፉን በማረጋገጥ አዳጊውን የህዝብ ፍላጎት መልሶ የተመጣጠነ እድገት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም የገለጹት አፈ-ጉባዔው፤ ክልሎችም ገቢያቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።
ከአገራዊ ለውጡ በፊት የመሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊነት ችግር የነበረበት በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል በፌዴራል የመሰረተ ልማት ተቋማት የስርጭት ዝግጅትና የጋራ ገቢ አስተዳደርና ማከፋፈያ ቀመር ጥናት መካሄዱ ተገልጿል።