ኢዜማ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሊያዘጋጅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሊያዘጋጅ ነው
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ማስፈጸሚያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ።
ፓርቲው ለምርጫው ማስፈጸሚያ፣ ወረዳዎችን ለመደገፍና ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማዕከል ደረጃ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል።
የፓርቲው አመራሮች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱአለም አራጌ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ጭላንጭል እውን እንዲሆን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ለማጎልበትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከወረዳ ጀምሮ ያሉ የፓርቲው አመራሮች በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ምርጫው ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንም አክለዋል።
ከዝግጅቶቹ ገቢ ማሰባሰብ አንደኛው መሆኑን ጠቅሰው ከማዕከል እስከ ወረዳ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውቀዋል።
ዴሞክራሲን እውን ማድረግ የምንችለው እያንዳንዱ ዜጋ በሚያደርገው ተሳትፎ መጠን ነው ያሉት አቶ አንዱአለም በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሩ ዜጎች አቅማቸው በፈቀደ መጠን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትክክለኛ ሚናቸውን እንዲወጡ ከሕዝቡ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ናቸው።
ዜጎች ለፓርቲው የሚያደርጉት ድጋፍ ምርጫ በማሸነፍ በሕዝብ የሚገራ መንግስት ለመመስረት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ፓርቲው ለቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ማስፈጸሚያ የተለያዩ መርሃ-ግብሮችን አዘጋጅቶ ከደጋፊዎቹ ገቢ ለማሰባሰብ ዝግጅት ማድረጉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የካቲት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚካሂደው የእራት መርሃ ግብር ከ10 ሺህ አስከ 50 ሺህ ብር የመግቢያ ትኬት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ኅብረተሰቡ በፓርቲው የባንክ ሒሳብ ቁጥርና በተለያዩ የድጋፍ ማድረጊያ ዘዴዎች ድጋፍ ማድረግ እንደሚችል ተገልጿል።