ቀጥታ፡

እርስ በእርስ በመተሳሰብና ከለውጡ ኃይል ጋር በመሆን ሰላማችንንና ልማታችንን እናስቀጥላለን....የምስራቅ ሃረርጌ ዞን ነዋሪዎች

ሀረር ጥር 28/2013 (ኢዜአ) እርስ በእርስ በመተሳሰብና ከለውጥ ኃይሉ ጋር በመተባበር የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ወጣቶችና ነዋሪዎች ገለጹ።

የዞኑ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን እና በአገሪቱ እየተከናወነ የሚገኘውን የልማት ጉዞ በመደገፍ ዛሬ ሰልፍ አካሂደዋል::

በዞን ደረጃ በደደር ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተገኙት ነዋሪዎች እንደገለጹት በአካባቢው የሚኖሩ የብሔር ብሔረሰቦች የእርስ በእርስ መደጋገፍ፣መተሳሰብና መቻቻልን በማዳበር ለሰላምና ለልማት እንደሚሰሩ ተናግረዋል::

ከቀረሳ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ አይሻ አብዱለጢፍ እንደገለጹት በአካባቢያቸው ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እንደ ከዚህ ቀደሙ እየተደጋገፉና እየተረዳዱ ሃገሪቱን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማሻገር የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።

በተለይ ከዚህ ቀደም በአካባቢው በሀሰት መረጃ ይከሰት የነበረው ግጭት በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት ማጣቱንና ህዝቡ መንቃቱን ተናግረዋል::

“ከመንግስት ጎን በአንድነት በመሆን የአገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርብናል” ያለችው እና ከዞኑ ጎሮ ሙጢ ወረዳ የመጣችው ወጣት መስከረም አለሙ “በተለይ እንደወጣትነታችን ሰርተን በመለወጡ ሂደት ላይ በትኩረት እየሰራን ነው” ብላለች።

“ጠላት ወጣቱን በተለያየ መንገድ መጠቀሚያ ማድረጉ የማይቀር እኩይ ተግባር ስለሆነ ከዚህ ድርጊት እራስን ማራቅ ይገባል” ብላለች::

ከቀርሳ ወረዳ የመጣው ወጣት ጀማል ተሺ በበኩሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት እንዲኖሩ ያደረገውን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከርና እሱም የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

“አፍራሽ ሃይሎች በፌስ ቡክና በሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚያሰራጩትን የተሳሳተና ለግጭት የሚዳርግ መልዕክት መቀበል አቁመናል፤ለማህበረሰቡም እውነተኛ መረጃ እያደረስን እንገኛለን”ብሏል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ባጭር ጊዜ ለውጥ ያስመዘገቡ ስከታማ ስራዎችን አከናውነዋል ።

የዞኑ ነዋሪዎችም አሁን ያስመዘገብነውን የሰላምና የልማት ጉዞን ወደ ተሻለ የማሳደግ ስራ ማከናወን ይጠበቅብናል” ያሉት አስተዳዳሪው “የለውጡ አደናቃፊ የሆኑትን የኦነግ ሸኔ እና ሌሎች ጸረ ልማትና ጸረ-ሰላም ሃይሎችን ተግባር በተደራጀ መልኩ መዋጋት ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ወጣቶች የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሴቶች አባ ገዳዎች የመንግስት ሰራተኞች አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም