ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያውን ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ሊሟሉ ይገባል - የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች

ጥር 28/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያውን ውጤታማ ለማድረግ የገበያ ሥርዓቱን የሚያሳልጡ መሰረተ-ልማቶች መሟላት እንደሚገባቸው የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች አሳሰቡ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቆት በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም እንዳለው ተገልጿል።

የካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሳምንት በቀረበበት ወቅት እንደተብራራው፤ የካፒታል ገበያ ለኅብረተሰቡ አማራጭ የቁጠባ መንገዶችን በማቅረብ የቁጠባ ምጣኔን ከፍ ያደርጋል።

ይህም ኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ፍላጎት በአገር ውስጥ ቁጠባ እንዲደገፍ በማድረግ ከውጭ ፋይናንስ ጥገኝነት ለመላቀቅ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑ ተመላክቷል።

መንግሥት ረጅም ዕድሜ ያላቸው የግምጃ ቤት ሠነዶችን በካፒታል ገበያ በመሸጥ ፋይናንሱን ለመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለማዋል እንደሚያስችለውም ተጠቁሟል።

በካፒታል ገበያ የድርጅቶቹን የአክሲዮን ዋጋ ተመን በማውጣት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታነት ለማዛወር አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ረቂቁ አዋጁ ይጠቅሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎችም በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መጀመሩ ወቅታዊና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ 'ከፍተኛ አስተዋጽኦ' አለው ብለዋል።

በተለይም የግልና የመንግሥት ተቋማት ፋይናንስ እንዲያገኙ ሰዎችም የአክሲዮን ባለቤት እንዲሆኑ  አማራጮችን በማስፋት እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።      

የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ተስፋዬ ኃይለሚካኤልና የሕግ ባለሙያው አቶ እሸቱ ኢረና ካፒታል ገበያ ለኢኮኖሚው እድገት ያለውን ሚና እንዲህ አስረድተዋል።

ያም ሆኖ የካፒታል ገበያው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ለዘርፉ የሚመጥን የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ ዝርጋታና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ሊኖር ይገባል ይላሉ።

የምጣኔ ኃብተ ባለሙያዎቹ አቶ ተስፋዬና አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው የካፒታል ገበያውን የሚመራ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማብቃትና ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉ መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጉታ ቴሶ ደግሞ የቴክኖሎጂ ሥርዓት፣ የኢንተርኔት አቅርቦትና የመረጃ አያያዝ አሁን ካለበት ደረጃ ሊጎለብት ይገባልም ነው ያሉት።

በረቂቅ አዋጁ ጤናማ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለመፍጠር ጠንካራና ተቋማዊ ነጻነት ያለው የካፒታል ገበያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንደሚቋቋም ተመላክቷል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተጠቀሰው ተቋሙ ጠንካራና ገበያውን በፍትሃዊነትና በግልጸኝነት የሚመራ መሆን እንዳለበትም አቶ እሸቱ ይናገራሉ።

ባለሥልጣኑ በሚያወጣቸው የአሰራር መመሪያዎች አጠቃላይ ሥርዓቱንና የቴክኒከ ጉዳዮችን በጥንቃቄ መከወን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።

እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ከወዲሁ ማሟላት ከተቻለ፤ የካፒታል ገበያው የአገሪቷን ምጣኔ ኃብት ለማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አቶ ጉታ ጠቁመዋል።

የካፒታል ገበያ እንደ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ተዛማጅ ውሎችና ወይም እነዚህን የመሰሉ የሠነድ መዋዕለንዋዮች ገበያ ሲሆን ሁለት አይነት ግብይቶችን ያስተናግዳል።

አንደኛው አዳዲስ አክሲዮኖች፣ ቦንዶች፣ የተስፋ ሰነዶችና ሌሎች የገንዘብ ሠነዶች በመሸጥ አዲስ ካፒታል የሚሰበሰብበት የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ ነው።

ሁለተኛ ደረጃ ገበያው ደግሞ የሰነድ መዋዕለንዋዮች በመጀመሪያ ደረጃ ገበያ ከወጡ በኋላ በጠቅላላ የኢንቨስተር ማኅበረሰብ የሚገበያዩበት ገበያ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም