የዓለም የጉዞና ጉብኝት ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የጉዞ ደህንነት ማረጋገጫ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም የጉዞና ጉብኝት ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የጉዞ ደህንነት ማረጋገጫ ሰጠ
ጥር 28/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የጉዞ እና ቱሪዝም ምክር ቤት የጉዞ ደህንነት ማረጋገጫ ዕውቅና ማግኝቷን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሒሩት ካሳው ምክር ቤቱ የሰጠውን የጉዞ ደሕንነት ማረጋገጫ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የቱሪዝም መስኩን ለማነቃቃት በርካታ ስራዎች ስታከናወን ቆይታለች።
በዚሁ መሰረት መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ያደረገው የዓለም የጉዞና ጉብኝት ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የጉዞ ደሕንነት ማረጋገጫ መስጠቱን ገልፀዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ምክር ቤቱ የጉዞ ደህንነት ማረጋገጫ ከሰጣቸው 14 የአፍሪካ አገራት አንዷ መሆን ችላለች።
የደህንነት ማረጋገጫው የተገኘው በቱሪስት መዳረሻዎች ላይ በተከናወኑ ተግባራትና ዘርፉ እንዲነቃቃና እንዲያገግም ስራቴጂ ተቀርጾ በመሰራቱ እንደሆነም አንስተዋል።
የማረጋገጫው መገኘት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም መስክ ቀድሞም እንዳልተዘጋ የገለጹት ሚኒስትሯ ማረጋገጫው መገኘቱ ደግሞ ጎብኚዎች ያለምንም የደህንነት ስጋት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ምክር ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ እውቅና ካላቸው ድርጅቶች ግንባር ቀደም መሆኑን ተናግረዋል።
ከ200 በላይ አባል አገራት ያሉት ይህ ምክር ቤት የጉዞ ደህንነት ማረጋገጫ እውቅናውን መስጠቱ የቱሪዝም መስኩ በሙሉ አቅም ስራ እንዲጀምር በማድረግ የራሱ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
በዓለም ላይ በኮቪድ-19 ምክንያት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በእጅጉ የተቀዛቀዘ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ንግድና ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ከፍአለ ናቸው።
የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን መልሶ ለማነቃቃት በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አማካኝነት መስኩን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።