ቀጥታ፡

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የፖለቲካ አመራሩ የቁርጠኝነት ማነስና የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ጉድለት ማነቆ መሆናቸው ተገለፀ

ጥር 28/2013 (ኢዜአ) ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስና የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ችግር ተግዳሮቶች ናቸው ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ የተቋማት ሃላፊዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ከተቋማት ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብና በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት በመሆኑ የተቋማት ቅንጅትና የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከፍተኛ አቃቤ ህግ አቶ አቤል ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት የችግሩን ስፋት ለመቀነስ ፍልሰትን ከልማት አጀንዳዎች ጋር አቀናጅቶ መተግበር ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ከታችኛው የፖለቲካ አመራር ጀምሮ የተቋማት ሃላፊዎችም ጭምር ችግሩን ለመፍታት የወጡ ፖሊሲዎችና ደንቦች ተግባራዊነት ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ስራ ትኩረት መስጠት አለባቸው

ስራውን የአንድ ወቅት አድርጎ የመመልከት ዝንባሌዎችም አሉ ያሉት አቶ አቤል ችግሩን ለመፍታት ያልተቋረጠ ክትትልና የህገ-ወጦችን ሰንሰለት በጣጥሶ ስደትን እስከ ማስቆም መቀጠል አለበት ብለዋል።

የዘርፉን ችግር በቀላሉ ለመፍታት በቂ የሰው ሃይል፣ ቴክኖሎጂን መጠቀምና ከአጎራባች አገራት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የፕሮግራም ማኔጀር የሆኑት ኢንስፔክተር ጉግሳ ገብረስላሴ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከአጎራባች አገራት ጋር እየተደረገ ያለው ስራ ውጤታማ እየሆነ ነው።

ነገር ግን ከችግሩ ውስብስብነትና ስፋት፣ የፖለቲካ አመራሩ ድጋፍ ውስንነት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ያለመስራት ውስንነቶች አሉ ብለዋል።

የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች በአግባቡ መተግበራቸውና ችግሩን ከስሩ ለመንቀል ከታችኛው የመንግስት መዋቅር ጀምሮ በጥምረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ህገወጥ የሰራተኛ ምልመላና መከላከያ ቡድን መሪ አቶ ዘርይሁን የሺጥላ የሃይማኖት አባቶች፣የመገናኛ ብዙሃንና ህብረተሰቡ የግንዘቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት መስራት አለባቸው ይላሉ።

በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይን አገራዊ አጀንዳ አድርጎ መስራት ይገባል ነው ያሉት። 

በዋናነትም የችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ወጣቶች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን በማጠናከርና የተጀመሩ የተቋማት ጥምረቶችን ውጤታማ በማድረግ ዜጎችን ከስቃይና ከእንግልት ማዳን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ፍልሰትን ከልማት አጀንዳዎች ጋር አቆራኝቶ የመሄዱ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የስራ ፈጠራ ባለሙያ አቶ አምሳሉ በሺ ናቸው።

በተለይ የተቋማት የበላይ ሃላፊዎችን የተቀረጹ አጀንዳዎች የማስተግበርና ህብረተሰቡን በማስተባበር የችግሩን ስፋት ለመቀነስ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ለውጤቱ ከአሰራርና አደረጃጀት ጀምሮ የተቀናጀና የተናበበ ሥራ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ መከወን እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም