ፓርኮችን ከአደጋ የመጠበቅ ሀላፊነት የሁሉንም ትኩረት የሚሻ ነው-- የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች - ኢዜአ አማርኛ
ፓርኮችን ከአደጋ የመጠበቅ ሀላፊነት የሁሉንም ትኩረት የሚሻ ነው-- የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች
ሀዋሳ ጥር 28/2013 (ኢዜአ)- በሀገሪቱ የሚገኙ ፓርኮችን ከጉዳት የመጠበቅ ሀላፊነት የሁሉንም ትኩረት የሚሻ ሊሆን እንደሚገባ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
በአርባምንጭ ከተማ የነጭሳር ብሄራዊ ፓርክን ከጉዳት ለመከላከል ታስቦ በተካሄደው መድረክ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ባለድርሻ አካላት እንዳሉት የፓርኮች ጉዳይ የጥቂት አካላት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን መሆኑን መረዳት ይገባል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንዳሉት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ብሄራዊ ፓርኮች ላይ የሚደርስ ጉዳት የዱር እንስሳቱንና ፓርኩን ብቻ ሳይሆን መላውን የአካበቢ ህዝብ ብሎም ሀገርን የሚጎዳ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የጉዳት ጫናው ያረፈው በነጭ ሳር ፓርክ ላይ ይሁን እንጂ ሌሎች ፓርኮችም ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
"የሀገር ሀብት የሆኑ ፓርኮችን ከጉዳት መጠበቅ ሁሉም የማይናቅ ሀላፊነትና ድርሻ አለው" ብለዋል።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው ደን የካርቦን ልቀትን በመከላከል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
"የበርካታ የዱር እንስሳት መጠለያ በመሆንም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ የአካባቢው ህብረተሰብ ጭምር ፓርክን ከጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱን አሻራ ማኖር እንደሚገባው አመልክተዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ክልሉ በርካታ ፓርኮች ያሉት ከመሆኑ አንጻር ከፍተኛ ስራ ይጠበቅበታል።
የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ብቻ ሳይሆን የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ፣ የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ፣ የሻላ አብያታ ፓርክና ሌሎችም ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የፓርኮችን ጉዳት ለመከላከል የኦሮሞ አባገዳዎች ምርጥ ተሞክሮ እንዳለ ተሞክሮውን መሰረት ባደረገ መልኩ በተለይ በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ እንደሚሰራ ተናግረዋል '
በፓርኩ የሰፈሩ ህገወጥ ሰፋሪዎችን በማስወጣት አስፈላጊውን ጥበቃ ለመድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ፓርኮችን ከጉዳት መጠበቅ የሚቻለው በክልሎችና ወረዳዎች በሚገኙ አካላት ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ታስቦ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የጠቆመው ደግሞ አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ነው።
"ስምምነት መፈረም ብቻውን ለውጥ አያመጣም፤ በውጪ ያሉ ፓርኮችን ማየት ቢቻል የሚተዳደሩት በህግና በህግ ብቻ ነው"ያለው ሻለቃ ሀይሌ መንግስት ህግ የማስከበር ስራውን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክቷል።
የሀይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ላይ የተደቀነው አደጋ በሌሎች ፓርኮችም ላይ የሚስተዋል መሆኑን ተናግረዋል ።
የፓርኮችን አደጋ ለመቀልበስ የፌዴራል መንግስት ብቻውን ሊያደርግ የሚችለው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
በፓርኮቹ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መላውን ህብረተሰብ ባሳተፈ መልኩ የክልል መንግስታት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የነጭ ሳር፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ማዜ፣ ቦረና፣ አዋሽ ጋምቤላ፣ ብሄራዊ ፓርኮችን በአፍሪካ የታወቀው አፍሪካን ፓርክስ የተሰኘው ፋውንዴሽን የፓርክ አስተዳደር ስራውን ለመስራት ቃል መግባቱን አስታውቀዋል።