አሜሪካ የኢትዮጵያን ጥልቅ ታሃድሶና ብልጽግና ለመደገፍ ላሳየችው ቁርጠኝነት ምስጋና እናቀርባለን ... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ የኢትዮጵያን ጥልቅ ታሃድሶና ብልጽግና ለመደገፍ ላሳየችው ቁርጠኝነት ምስጋና እናቀርባለን ... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ጥር 28/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ለማሳካት የምታካሂደውን ጥልቅ ታሃድሶ ለመደገፍ አሜሪካ ላሳየችው ቁርጠኝነት መንግስት ምስጋናውን ያቀርባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይሄን ያሉት ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብልንኬን ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብልንኬን ጋር የኢትዮጵያንና የአሜሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ፣ በመጪው ምርጫና በቀጠናው ሰላምና ደህንነት ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ለማሳካት የምታካሂደውን ጥልቅ ተሃድሶ ለመደገፍ አሜሪካ ላሳየችው ቁርጠኝነት ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።
በዴሞክራሲ የበለፀገችና ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባትና የጋራ ብልጽግናን ለማሳካት የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጠናከረ ሁኔታ መጓዝ እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቲውተር ገጻቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እያደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ በቂና ቀጣይነት ያለው ሊሆን እንደሚገባ በውይይታቸው ወቅት ማንሳታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረገጽ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።