ቀጥታ፡

ወንድማማችነትን ለማጠንከርና መተሳሰብን ለማጎልበት የሃይማኖት አስተምህሮን በተግባር ማሳየት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2013(ኢዜአ)  ልዩነቶችን በመተው ወንድማማችነትን ለማጠንከርና እርስ በእርስ መተሳሰብን ለማጎልበት የሃይማኖት አስተምህሮን በተግባር ማሳየት እንደሚገባ ተገለፀ።

በግብጽ የታላቁ አል-አዝሃር ኢማም አህመድ አል-ታይብ እና የቫቲካን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ /ፖፕ ፍራንሲስ/ ለዓለም ሰላምና አብሮ ለመኖር የሚያስችል የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ እ.አ.አ በየካቲት 4 ቀን 2019 አቡዳቢ ውስጥ በተካሄደ ስብስባ ተፈራርመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በቅርቡ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኗል።

በኢትዮጵያም የሃይማኖት አባቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ቀኑን በማስመልከት ዐውደጥናት ተካሂዷል።

ዐውደ ጥናቱን አሜን ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ "ስለ አንድነት፣ መተባበር፣ መተጋገዝ እንጂ በብሔርና በሌላም መለያየት እንደማይገባ የሃይማኖት አስተምህሮ ይነግረናል" ሲሉ ነው በመድረኩ የገለጹት።

ሆኖም በምድር ላይ ጥቅምና ስልጣንን መሻት እንዲሁም ፈጣሪን አለማወቅ ደም ለመፋሰስ፣ ለእርስ በእርስ መገዳደልና ለመጣላት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

የሰው ልጅ ጊዜያዊና ጠፊ መሆኑን መዘንጋቱ፣ ሞትን ማወቅ እንጂ አለማመኑ እርስ በእርስ ለመጠፋፋት መንስኤ እንደሆነውም ተናግረዋል።

ወንድማማችነትና እህትማማችነት ፈጣሪ የሚወደው በቅዱሳን መፃህፍት የተገለፀ ቢሆንም ተግባሩ ግን ለሰው ልጆች ከብዶ እንደሚስተዋል ነው ተቀዳሚ ሙፍቲው በአጽንኦት የገለጹት።

"ስለሆነም እንመለስ፣ ፈጣሪያችንን እንወቅ፣ ያወቅነውንም ተግባራዊ እናድርግ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው "አገሪቱ በሃይማኖት ብዝሃነትና ትብብር የምትታወቅ ከመሆኗ አኳያ የወንድማማችነት እህትማማችነት ፅንሰ ሃሳብ ትልቅ ዋጋ አለው" ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የብሔርና የሃይማኖት ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ የዜጎች የእርስ በእርስ መጠፋፋትና ከቀዬ መፈናቀል ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸው "ይህ የረጅም ዘመን ተከባብሮና ተደጋግፎ አብሮ ከመኖር ባህል ጋር አብሮ አይሄድም" ብለዋል።

"የወንድማማችነትና እህትማማችነት ትስስር ከነጠላ ግለሰቦች እርካታ ድምር የላቀ ነው" ያሉት ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፣ አሁንም ከጎሳና ከብሔር፣ ከራስ ሃይማኖት እርካታ ይልቅ የሰው ልጅ ሁሉ እርካታ ብሎም የአገር ሰላምና ብልዕግና የበለጠ መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዐውደ ጥናቱ የተሳተፉት ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው በአገሪቷ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች አማኝ ማህበረሰብ ካለባት አገር የማይጠበቅና ልብ የሚሰብር ነው ብለዋል።

"እየሆነ ያለው ነገር ከእኛነታችን የማይጠበቅ ነው" ያሉት ኡስታዝ አቡበከር ቤተ-እምነቶች አማኞቻቸው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው ችግር የሚመነጨው በሁሉም ዘርፍ የበላይነት አግኝተው እየመሩ ያሉ አካላት የተሟላ እውቀት፣ ብቃትና ስብዕና ከማጣታቸው መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢሳት ሥራ አስኪያጅ አንዳርጋቸው ጽጌ ናቸው።

የሰብዓዊነት ችግር የሚስተዋለውም ነገሮችን አሻግረው ማየት በተሳናቸው አካላት መሆኑን አንስተው "ይህን ለመቀየር የበላይነት የያዙትን አካላት አስተሳሰብ በመቀየር አሊያም የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸውን በቦታው በማስቀመጥ ነው" ብለዋል።

ህብረተሰቡ ሰላሙን ሊያደፈርሱ የሚፈልጉ አካላትን አይሆንም ብሎ ሊቃወም እንደሚገባም ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም