ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የሚነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ የሚነሱ ችግሮች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው አቋም ይዛለች ብለዋል።

እስካሁን ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር በተካሄደው ውይይት በተለይም የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የግድቡን ውሃ በሦስት ዓመታት መሙላት ቢገባትም ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ማራዘሟን ጠቅሰዋል።

ያም ሆኖ በውይይቶቹ በኢትዮጵያ የወደፊት የመልማት መብት ላይ ጫና የሚያሳድሩ ጉዳዮች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።  

በሦስቱ አገራት የመርህ ስምምነት አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 ውሃ ሙሌትን በተመለከተ በቅድሚያ መግባባት እንደሚያስፈልግ ኢትዮጵያ አቋም መያዟንም ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከቱ የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየት እንደሚገባ ተናግረዋል።  


ለዚህም ሁለተኛው የውይይት ምዕራፍ ከባድና ከግድቡ ውጪ ያሉ ሕጎችን መፈተሽ የሚጠይቅ መሆኑን  አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት የሚካሄደውን ድርድር አንድም ጊዜ አላስተጓጎለችም ያሉት ሚኒስትሩ  አስተጓጉላለች ተብሎ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት የሚነሳው ወቀሳ ትክክል አይደለም ብለዋል።

እንዲያውም ኢትዮጵያ በሕብረቱ አደራዳሪነት ውይይቱ እንዲቀጥል እየሰራች መሆኑንና ያም ሆኖ ሱዳን ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ውይይቱ ሰባት ጊዜ እንዲቋረጥ ማድረጓን ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያ አሁንም ግድቡን በተመለከተ የሚነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ በሂደቱ የኢትዮጵያን ቀጣይ የመልማት መብት የሚጻረር ማንኛውንም አይነት አንቀጽ በሕግና ደንብ ውስጥ ማካተት ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ ግድቡ በቀጣናው የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚካሄድ ፕሮጀክት መሆኑንም አስረድተዋል።

በአገሪቷ 65 ሚሊዮን ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደማያገኙ ጠቅሰው ግድቡ ይህንን ችግር በማቃለል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት በሚኖርበት ወቅት ለጎረቤት አገራት ሃይል ለማቅረብ ውጥን መኖሩን ተናግረዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ለሱዳን 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደምታቀርብና ከጅቡቲ ጋርም በተመሳሳይ ትስስር መፈጠሩን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም