ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 200 ኦፊሰሮች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 200 ኦፊሰሮች አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ጥር 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ያሠለጠናቸውን 200 ኦፊሰሮች አስመረቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ለሁለት ወራት ያሰለጠናቸውን የአቪዬሽን ደህንነት ሙያ ጀማሪ ኦፊሰሮችን በዛሬው ዕለት ባስመረቀበት ወቅት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመሰገን ጥሩነህ እንደተናገሩት፤ ተመራቂዎቹ የአገር ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርገውን የተሳካ ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ይኖራቸዋል።
ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ያካበተውን የረጅም ጊዜ ልምድ በመቀመር ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅቶ ስልጠና መስጠት መጀመሩ የሚያኮራ የለውጥ ተግባር መሆኑን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።
“ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የአቪዬሽን ደህንነት ባለሙያዎችን ዓለም አቀፍ መሥፈርት በጠበቀ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ማሠልጠኑ ኢትዮጵያን በዘርፉ ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር አቅም ይፈጥራል” ብለዋል።
ተመራቂዎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች የተመለመሉና በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ቆይታቸውም ለሁለት ወራት በአቪዬሽን የደህንነት ኪነሙያ ስልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት ተበርክቷላቸዋል፡፡
ተመራቂዎቹ የተሠጣቸው ስልጠና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርገውን የተሳካ ጉዞ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አቶ ተመስገን አመልክተዋል፡፡
በአቪዬሽን ዘርፉ አገልግሎታቸውም ትህትናን፣ እውቀትን፣ ክብርንና ታማኝነትን በመላበስ አገራቸውንና ህብረተሰባቸውን ማገልገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የአቪዬሽን ደህንነት ባለሙያዎቹ በአገሪቱ ላይ ሊቃጣ የሚችል የሽብር ጥቃትንና የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመመከት በኩል የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነትና የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ዳይሬክተር ጀነራሉ አሳስበዋል።
የብሄራዊ መረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በአቪዬሽን ደህንነት መስክ ጥራት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት፤ ተጨባጭ፣ ዘመናዊና ወቅታዊ እንዲሁም አካበቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ሥልጠና በመስጠት የዘርፉን የአገልግሎት ብቃት ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ባገኘው እውቅና መሠረት በደህንነት፣ በኢንተለጀንስ፣ በስትራቴጂክ ጥናትና በቋንቋ የትምህርት መስኮች በዲግሪና በዲፕሎማ ስልጠና ለመስጠት ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አቶ ወንድወሰን አያይዘው ማብራራታቸውን አገልግሎቱ ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያሳያል።
ብሄራዊ የመረጃ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃና ደህንነት መስክ ስልጠና በመስጠት ከአርባ አመታት በላይ የዘለቀ ልምድ ያለው ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማደግ ችሏል።