ቀጥታ፡

በወጪ ንግድ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ተባለ

አዲስ አበባ ሀምሌ 18/2010 በወጪ ንግድ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለው የለውጥ ሂደት የወጪ ንግዱን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ እየፈጠረ መሆኑም ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ባለፉት ዓመታት ማህበሩን በቦርድ አመራርና አባልነት ላገለገሉ ግለሰቦች የምስጋናና እውቅና መስጠት ፕሮግራም ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት፤ መንግስት የአገሪቱ የወጪ ምንዛሬ ግኝት ወሳኝ ምንጭ የሆነውን የወጪ ንግድን ማሳደግ የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ በመውሰድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ውጪያዊ እና ውስጣዊ ተግዳሮቶች  የወጪ ንግድ ስራ አፈጻጸማችን የታቀደውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ ላይ የሚታዩትን ችግሮች መፍታት ይቻል ዘንድ ዘርፉን  ከሚወክሉ ማህበራት ጋር በትብብር መስራት የሚኒስቴሩ ዋና ተግባር ሆኖ እንደሚቀጥል አቶ መላኩ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ወጪ ንግድ/ኤክስፖርት/ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ጋር ያለውን የትብብር ግንኙነት እንዲጠናከር የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ መላኩ አያይዘውም የማህበሩ አባላትና ላኪ ድርጅቶች በወጪ ንግድ ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በዋጋ፣ በጥራትና በማስረከቢያ ጊዜ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል። ላኪዎች ከሚገዙ ድርጅቶች ጋር የሚገቡትን ውል በማክበር የኩባንያዎቻቸውንና የአገራቸውን መልካም ስም በማስጠበቅ አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲችሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የንግድ ሥርዓቱን የሚያዛቡ ሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትርባንድ እንቅስቃሴዎችን፣ የምርት ጥራት መጓደል ችግሮችንና የውጪ ምንዛሬ ግኝትን የሚጐዱ ተግባራትን ለማስወገድ ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ አቶ መላኩ ጥሪ አቅርበዋል። በአገሪቱ የሚስተዋለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት የወጪ ንግዱን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ መሆኑም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል።   በተለይም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት ስራ መጀመር፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባልነትና አዳዲስ የወደብ አገልግሎት አማራጮች መፈጠር ከዚህ አንፃር የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ እየተሻሻለ መምጣትና በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውር ላይ እየተወሰዱ ያሉት ውጤታማ እርምጃዎችም ለወጪ ንግዱ መነቃቃት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች መሆናቸውም ተጠቅሷል። በመሆኑም እነዚህን መልካም እድሎች በመጠቀም የወጪ ንግዱን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም