ኢዜአ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ራሱን ማሳደግና ማስተዋወቅ አለበት - የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ራሱን ማሳደግና ማስተዋወቅ አለበት - የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ጥር 27 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ራሱን ሊያሳድግና ሊያስተዋውቅ እንደሚገባው የተለያዩ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተናገሩ።
'በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን' ራዕይ የሰነቀው ኢዜአ፤ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታው ላይ ከፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተቋሙ የዕድሜውን ያህል ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመራቸውን ስራዎችና የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ግቦች አድንቀዋል።
ኢዜአ የቀደመ ተጠቃሽ የመረጃ ምንጭነት ዝናውን በማስመለስ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ አሁን በጀመረው መንገድ ራሱን ማጠናከር እንደሚገባውም ተናግረዋል።
ኢዜአ ፈርጀ ብዙ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ራሱን በማስተዋወቅ ረገድ ክፍተት እንዳለበት ገልጸው፤ በፕሮሞሽን ላይ ሊሰራ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ኢዜአ የሁሉም ሚዲያዎች መረጃ መጋቢ በመሆኑ እንደ አንድ ተቋም እንደማይታይ የገለጹት ባለሙያዎቹ፤ በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ላይ የይዘት ብዝሃነት እንዲኖረው የዘመኑን የማህበራዊ ሚዲያ ተግዳሮት ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በየሙያ ዘርፉ ጋዜጠኞችን ማሰልጠን፣ የስራ ዝርዝር በማውጣት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ባለሙያዎቹ ተወክለው የመጡባቸው ተቋማት ኢዜአ በሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በባለሙያዎቹ የተሰጠው ግብዓት ጠቃሚ መሆኑንና ከአጋር ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚያስችለውን ፍኖተ ካርታ ዘርግቶ ወደ ስራ መግባቱንም አብራርተዋል።
ኢዜአ ከመንግስትም ሆነ ከግል መገናኛ ብዙሃን ጋር መልካም ግንኙነት ፈጥሮ በአገራዊ ጉዳዮች ለአብነትም በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በመግባባት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
በአገር ገጽታ ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና የሃሰተኛ መረጃ ቀውስን ለመከላከል የመረጃ ክፍተትን ለመሙላት ኢዜአ ትልቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
በመሆኑም ቀደም ሲል የተመጣበትን መንገድ በማሻሻል አጋር አካላት ከኢዜአ ጋር ትብብርና ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የኢዜአ ቢዝነስ ልማትና ሀብት አስተዳድር ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ ኢዜአ ከዜናና ዜና ነክ ስራዎች በተጨማሪ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ወሩ የሚያሳትመው መጽሄት እንዳለው ገልጸዋል።
ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ጥራት ያላቸው የህትመት ውጤቶችን ለደንበኞቹ እንደሚያደርስም አረጋገጠዋል።
የኢዜአ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ ከ18 ሚዲያዎች ጋር ስምምነት በማድረግ መረጃ እየመገበ የሚገኘው ኢዜአ 'እንደ ብዙ ተቋም የሚቆጠር ነው' ብለዋል።
አጋር ተቋማት ከኢዜአ ጋር ቢሰሩ ሀብት፣ ጉልበትና ጊዜ እንደሚቆጥቡና የመረጃ መዛባት እንዳይፈጠርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።