ለጤናማ እናትነት መረጋገጥ ከ180 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ወጪ ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል- የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለጤናማ እናትነት መረጋገጥ ከ180 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ወጪ ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል- የጤና ሚኒስቴር
ሐዋሳ፣ ጥር 27/2013 (ኢዜአ) የእናቶችንና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሕይወት አድን መድሐኒቶችና ግብአቶች ተደራሽ ማድርጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
15ኛው ሃገር አቀፍ የጤናማ እናትነት ቀን በሲዳማ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በዚህ ወቅት በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም እንደገለጹት የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ እና የደም መፍሰስ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየተሠራ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት በተካሄደው እንቅስቃሴ የወሊድ አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ የሕይወት አድን መድሐኒቶችና ግብአቶች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የደም መፍሰስ ምላሽ ፓኬጅ መመሪያ በማዘጋጀት ከ110 በላይ ሆስፒታሎች መለስተኛ የደም ባንክ በማቋቋም የኦፕራሲዮን አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉንና የትራንስፖርት ችግሩን ለማቃለል ከ3 ሺህ 100 ባለይ አምቡላንሶች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
“ሆኖም ከመንገድ መሠረተ ልማቶች ችግር ባሻገር በየወረዳዎች ለጤና አገልግሎት የተሰጡ አምቡላንስ መኪናዎች ላልተገባ አገልግሎት ሲውሉ እየተስተዋለ በመሆኑ በአፋጣኝ የሚመለከታቸው አካላት ሊያርሙ ይገባል” ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለምጸሐይ ጳውሎስ በበኩላቸው “የጤናማ እናትነት ቀን ሲከበር ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ እናቶችን ለመታደግ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል”ብለዋል።
ከእናቶች ሞት መንስዔዎች ውሰጥ 50 በመቶ የሚከሰተው በደም መፍሰስ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ደግሞ ያልተደራጀ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ፣በግንዛቤ እጥረት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ወደ ህክምና ተቋም አለመውሰድ እና የአምቡላንስ ትራንስፖርት እጥረት ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።
“በሃገር ደረጃ በተደረገው ጥናት መሠረት በጤና ተቋማት የሚወልዱት እናቶች 65 በመቶ ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎች ወደ ጤና ተቋማት ሳይመጡ እቤታቸው ስለሚወልዱ ለሞት የመጋለጥ ዕድሉን ሰፊ ያደርገዋል”ብለዋል።
በመሆኑም የቤተሰብ፣የማህበረሰብና የሃገር ምሶሶ የሆኑትን እናቶች ሞት ለመከላከል ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ በመነሳሳት ሊታደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ መንግስት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና፣ የጤና ተቋማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍና መሰረተ ልማት አደረጃጀት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀው ይህም በቂ ስላልሆነም መንግስታዊ ያልሆኑ አደረጃጀቶች ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
“በ2030 ከእናቶች ሞት ነጻ የሆነች ሃገር ለመገንባት የተጣለውን ግብ ለማሳካት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እንዲሳኩ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል፡።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ ዮሐንስ ላታሞ “ ተገቢውን አገልግሎት በማቅረብ የእናቶችን ሞት መቀነስ የሞራልና የሰብአዊነት ጉዳይ ነው”ብለዋል።
“በመሆኑም ለእናቶች ሞት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የቤተሰብ አባዋራ ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባልም” ብለዋል።
በደም መፍሰስ ምክንያት እናት ለምን ትሙት በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሲዳማ ክልልና ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተካፍለዋል።