ቀጥታ፡

አንጋፋው የዜና ምንጭ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የብሮድካስት አገልግሎት ለመጀመር አቅዷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 27 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከዜና ምንጭነቱ ባሻገር የሳተላይት ብሮድካስት አገልግሎት በመጀመር የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ኢዜአ ላለፉት 79 ዓመታት ብቸኛው የአገሪቷ የዜና ምንጭ በመሆን እያገለገለ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ፣ የዕድሜውን ያህል ግን ያልተራመደ፣ ከመፍረስም ጫፍ ደርሶ የዳነ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም ነው።

ድርጅቱ ከቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ስር ወጥቶ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ ራሱን ከቻለ በኋላ ትልቅ አገራዊ ተልዕኮ ይዞ ዳግም በአዋጅ ተቋቁሟል።

በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕይ የሰነቀው ኢዜአ፤ በአገልግሎቱ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በአገራዊ ገጽታ ግንባታ፣ በብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ መግባባትና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ሕዝባዊ አጀንዳዎች ላይ በስፋትና በጥራት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታም አዘጋጅቷል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሠይፈ ደርቤ እንደሚሉት፤ ኢዜአ በዜናና ዜና ነክ፣ በፎቶና በዘጋቢ ፊልም፣ በሕትመት፣ በስልጠናና ማማከር ስራዎች ተደራሽነቱን እያሰፋ ነው።

ከፍኖተ ካርታው ዕቅዶች መካከል የራሱ የብሮድካስት አገልግሎት ለመጀመር ማቀዱን ገልጸው፤ ለዚህም በማቋቋሚያ አዋጁ ሕጋዊ መሰረትና መንግስታዊ ድጋፍ እንዳለው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በወራት ውስጥ ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ እየተደረጉ መሆኑን ያነሱት አቶ ሰይፈ፤ በዓመታት ውስጥ በሳተላይት ብሮድካስት አገልግሎት ለመጀመር አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ ነው የጠቀሱት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የዜና አገልግሎቶች የራሳቸውን ስራዎች አየር ላይ የሚያውሉበት አሰራርና አፈጻፀም እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ኢዜአ በኦንላይን የጀመራቸው የኤሌክትሮኒክስ ስራዎች አየር ላይ እንደሚያውል ገልጸዋል።

ድርጅቱ 3 ዘመናዊ የቴሌቪዥንና 4 የራዲዮ ስቱዲዮዎች ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንና አስፈላጊ ግብዓቶች በማሟላት በ10 ዓመታት ውስጥ ወደብሮድካስት አገልግሎት እንደሚገባ ነው ያረጋገጡት።

ኢዜአ ከዜና ምንጭነቱ ባሻገር ወደ ብሮድካስት አገልግሎት መግባቱ በአገር ውስጥና በውጭ የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት ብሎም አገራዊ ገጽታ ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ላይ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

የብሮድካስት አገልግሎቱ በይፋ እስኪጀመር የጀመራቸውን ወቅታዊ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች አጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ ይህንንም በተለይ ቅደመ ምርጫ ላይ በስፋት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም