ቀጥታ፡

በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መኖር የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ያሳድጋል -አቶ መላኩ አለበል

ጎንደር ፤ጥር 27/2013 (ኢዜአ) በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መኖር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን አካሄድ በማቀላጠፍ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እንደሚያሳድግ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጎንደር ከተማ ያቋቋመው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል ዛሬ በተመረቀበት ወቅት የተገኙት ሚኒስትሩ እንዳሉት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ሃገራዊ ምርትን በተሻለና ተወዳዳሪ በሆነ የገበያ ዋጋ በማቅረብ የወጭ ንግዱን ለማቀላጠፍ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት ከወጭ ንግድ ከተገኘው 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የግብርና ምርቶች ድርሻ 2 ነጥብ 33 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በተመቻቸባቸው የሃገሪቱ ክልሎች አርሶ አደሩ ወቅታዊ የዋጋ መረጃ ከማግኘት ጀምሮ በቅርበት በመገበያየት ካላስፈላጊ ውጣ ውረድና እንግልት እንዲላቀቅ ማገዙን ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት አምራቹና ገዢውን ከማገናኘት በዘለለ ለአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስተማማኝ የግብርና ግብአቶችን ለማቅረብ ሰፊ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ይህንን በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በዓይነትም ሆነ ብዛት ለማቅረብ ምርታማነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰሊጥን የመሰሉ የግብርና ሰብሎች በስፋት ከሚመረትባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ክልሉ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

ምርት ገበያው ያቋቋመው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል ለአምራቹና ባለሀብቱ ሰፊ የገበያ እድል የሚፈጥር በመሆኑ የክልሉ መንግስት ለማዕከሉ መጠናከር ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በክልሉ ተጨማሪ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ጠቁመው፤ ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ ማናቸውንም ድጋፍ ለምርት ገበያው ለማድረግ የክልሉ መንግስት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ አስተዳደሩ ለግብይት ማዕከሉ 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 2ሺ ካሬ ሜትር የግንባታ ቦታ በነጻ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በ14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጭ የተቋቋመው ዘመናዊ የኤልክትሮኒክስ ግብይት ማዕከል በሀገሪቱ አራተኛው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ናቸው።

ማዕከሉ 12 ዓይነት የግብርና ምርቶችን ለማገበያየት እንደሚያስችል አመልክተው በአንድ ጊዜም 90 የሚደርሱ ገዢና ሻጮችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።

በልማዳዊው የግብይት ሥርዓት ገዢዎች ምርታቸውን ከተረከቡ በኋላ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ገንዘባቸውን ሳያገኙ ይቆዩ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በሰሊጥ ማምረት የተሰማሩት አቶ ሙሉአለም ምልምሌ ናቸው፡፡

ምርት ገበያው ባቋቋመው የግብይት ማዕከል ዛሬ የሸጡትን ምርት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ገንዘባቸውን በባንክ በኩል በመረከብ ፍትሃዊ የግብይት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚችሉ መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ባለሀብት አቶ ተመስገን ሰጥአርጌ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን እያመረቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የግብይት ማዕከሉ ጎንደር ላይ መቋቋሙ አዲስ አበባ በመሄድ የሚደርስባቸውን እንግልትና ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል፡፡

በምረቃው ሥነሥርዓት ወቅት ለማዕከሉ ግንባታ መሳካት የጎላ አተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ምርት ገበያው በከተማው እያስገነባው የሚገኘው የግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘንም ተጎብኝቷል፡፡

የፌደራል ፣ ክልልና ጎንደር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ባለሀብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በማዕከሉ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም