ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚያሳድግ ፖሊሲና ስትራቴጂ እየተተገበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የብሔራዊ ትራንስፖርት ፖሊሲና ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ እየተተገበረ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

የሞጆ ደረቅ ወደብን ወደ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከልነት ማሸጋገር የሚያስችሉና ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሆነባቸው የወደብ መሳሪያዎች ምረቃና ስራ የማስጀመር ስነ-ስርዓት ተካሄዷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስና የዓለም ባንክ የቀጣናው ተወካይ ኡስማኔ ዳዮኔን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የንግድ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ደካማ መሆን አገሪቷ ከመስኩ የምታገኘው ገቢ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሆን አድርጎታል።

ችግሩን ለመፍታት የማሪታይም ባለስልጣን በዓለም ባንክ የሚደገፍ የንግድ ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ አቋቁሞ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ የሞጆ እና የኢትዮ-ጅቡቲን የንግድ አፈጻጸም ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ ነው።

የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆነው የመጀመሪያ ዙር የሞጆ ደረቅ ወደብ መሳሪያዎች የምርቃት ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

መሳሪያዎቹ የእቃዎች ማንሻ፣ ማጓጓዣ፣ ባዶ ኮንቴይነር ማስተናገጃ፣ ተርሚናል ትራክተርና መሰል መሳሪያዎችን ያካተቱ ናቸው።

ወደ ሥራ ለገቡት 47 መሳሪያዎች ግዥ ወጪ የሆነው ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከዓለም ባንክ በብድር የተገኘ ነው።

የመሳሪያዎቹ ወደ ሥራ መግባት በመስኩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን በንግድ ሎጂስቲክስ መስክ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጎን ለማሰለፍ የብሔራዊ ትራንስፖርት ፖሊሲና ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ እየተተገበረ ነው።

ይህንን ወደ መሬት ለማውረድም የሎጂስቲክስ ምክር ቤትና የትራንስፎርሜሽን ቢሮ መቋቋሙን ጠቁመዋል።

''ዛሬ የምናስመርቃቸው መሳሪያዎች የወደቡን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ትልቅ ፋይዳ አላቸው'' ያሉት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ ጊዜ ወጪና አስተማማኝነትን በማሻሻልም ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብን ወደ ሎጂስቲክስ ማዕከልነት ለማሸጋገር የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚካሄዱ የተናገሩት ደግሞ በማሪታይም ባለስልጣን የንግድ ሎጂሲቲክ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ ኃይለማሪያም ናቸው።

በዚሁ መሰረት የኮንቴይነር ጭነት ማስተናገጃ ጣቢያ፣ የጥቅልና ተያያዥ ጭነቶች ማቆያ፣ ደረቅ እቃዎች ማከማቻ መጋዘንና የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ለመገንባት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በወደቡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

የሞጆ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በበኩላቸው የሞጆ ደረቅ ወደብ ሎጂስቲክስ ማዕከል አገልግሎቱን ከማቀላጠፍ ባሻገር ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድም ምሳሌ የሚሆን ተግባር ማከናወኑን ገልፀዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም