ቀጥታ፡

የደቡብ ኮሪያ መንግስት ለስደቶችና የድርቅ ተጎጂዎች የ13 ሚሊዮን ዶላር የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ

አዳማ ሃምሌ 18/2010 የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞችና የድርቅ ተጎጂዎች የሚውል የ13 ሚሊዮን ዶላር የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ። ትናንት በአዳማ ከተማ ድጋፍ የተደረገው የ15 ሺህ ሜትሪክ ቶን አልሚነት ያለው ሩዝ በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ነው። የእህል ድጋፉን በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሚስተር ፓርክ ኢል የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይና በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተጠባባቂ ተጠሪ ለሆኑት ሚስተር ፖል ተርንቡል አስረክበዋል። ሚስተር ፖል በበኩላቸው ድጋፉን ለስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር አቶ እዮብ አወቀ በመፈራረም አስረክበዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሚስተር ፓርክ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገራቸው መንግስት የተደረገው ድጋፍ ለስደተኞቹ መሰረታዊ ፍላጎት ለሟሟለት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ ነው። "ኢትዮጵያ ለስደተኞች ክፍት የሆነ ፖሊሲ መከተሏ የሚያስመሰግናት ነው" ያሉት አምባሳደሩ በቀጣይም በአገራቸው በኩል ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል። በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተጠባባቂ ተጠሪ ሚስተር ፖል ተርንቡል በበኩላቸው በኮሪያ መንግስት የተደረገው የ13 ሚሊዮን ዶላር የምግብ ድጋፍ ለ25 ሺህ ስደተኞችና 500 ሺህ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ድርቅ ተጎጂዎች የሚውል ነው። የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር አቶ እዮብ አወቀ በበኩላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት የመጡ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች። በተለይ ለስደተኞቹ ለዕለት ኑሯቸው የሚያስፈልገው የእህል ቀለብ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት የሚቀርብ መሆኑንና የአሁኑ ድጋፍም የእዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል። "15 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሩዝ ከደቡብ ኮሪያ መንግስት በዓይነት ድጋፍ ስናገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው" ብለዋል። ድጋፉ ስደተኞች ያለባቸውን የምግብ ችግር በማቃለል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፣ "በእርዳታ ከተሰጠው ሩዝ ለስደተኞች የሚሆነው በቅርቡ ለ27 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይከፋፈላል" ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም