በጋምቤላ ከተማ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን ለማፋጠን አመራሩ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል...ኢንጂነር አይሻ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን ለማፋጠን አመራሩ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል...ኢንጂነር አይሻ አህመድ
ጋምቤላ፤ጥር 27/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን ለማፋጠን አመራሩ ህዝቡን በማሳተፍ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የከተማ ልማትና ኮንስትራከሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ አህመድ ተናገሩ።
ሚኒስትሯ ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በከተሞች ተቋማዊ መሰረተ ልማት መረሃ ግብር በጋምቤላ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ኢንጅነር አይሻ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የከተማውን መሪ ፕላን በጠበቀ መልኩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ተደራሽነት ለማረጋገጥና ከተማውን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ አመራሩ የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የከተማውን እድገት ለማፋጠን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ ቢሆንም፤ በተለይም በፕሮጀክቶች አፈፃፀም የሚታዩት ክፍተቶች የአቅምና የበጀት ውስንነት ብቻ ሳይሆን የጌጠኛ ድንጋይ ግብዓቶች በአካባባቢው ካለመኖሩ ጋር የተያያዘ መሆኑንም አመልክተዋል።
"በአፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ክፍቶችን በመለየት በቀጣይ በጋራ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በትኩረትና በቅንጅት ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለፕሮጀክቶቹ መሳካት በበጀትም ሆነ በሰው ኃይል የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኢንጂነር አይሻ አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ክልል የከተሞች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸንኳት ቾት በበኩላቸው "የከተማው የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ስራዎች የተጓተቱት ህግና መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ፕሮጀክቶች ለተቋራጮች ሲሰጡ ስለነበር ነው" ብለዋል።
ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የተቀናጀ አሰራር በመፍጠር ቀደም ሲል የታዩ ችግሮችን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ በዘርፉም የተሻሉ አፈፃፀሞች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በከተማው ቀበሌ 03ና 01 በከተሞች ተቋማዊ መሰረተ ልማት መረሃ ግብር በመገንባት ላይ የሚገኙ መንገዶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።