ኢትዮጵያና ሱዳንን ወደ ግጭት በማስገባት በአካባቢው ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሹ አካላት ፍላጎት እንደማይሳካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሱዳንን ወደ ግጭት በማስገባት በአካባቢው ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሹ አካላት ፍላጎት እንደማይሳካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27 /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሱዳንን ወደ ለየለት ግጭት በማስገባት አገሮቹን አዳክሞ በአካባቢው ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሹ አካላት ፍላጎት እንደማይሳካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር እ.አ.አ በ1902 ዓ.ም ስምምነት የተወሰነ ሲሆን ሻለቃ ግዊን የተባለ እንግሊዛዊ ቀያሽ ድንበሩን ለብቻው በ1903 አካሎ ነበር።
ሻለቃ ግዊን የድንበር ማካለሉን ያካሄደው ያለ ኢትዮጵያ ተወካይና ዕውቅና ብቻውን በመሆኑ የድንበር ማካለሉ ሪፖርት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተቀባይነት አላገኘም ነበር።
የማስታወሻ ልውውጡን የሱዳን መንግስት ያጸደቀው መሆኑንም ለአፍሪካ ህብረት በዚያው ወቅት አሳውቋል።
ሆኖም ሱዳን በሁለቱ አገሮች መካከል ድርድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ በመሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተከብሮ እንዲቆይ የሚደነግገውን ስምምነት በመጣስ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ገብታለች።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ ለህግ ማስከበር መሰማራቱን ተከትሎ የሱዳን ጦር ሰራዊት በከባድ መሣሪያ በመደገፍ የተደራጁ ጥቃቶችን ፈጽሟል።
በዚህም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላም እና በመነጋገር ለመፍታት ዝግጁነቷን በተለያየ ጊዜያት እያሳወቀች ቢሆንም አገሮቹን ወደ ለየለት ግጭት ለማስገባት የሚፈልጉ አካላት ጉዳዩን የበለጠ እያጮሁት እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በወቅታዊ የኢትዮ-ሱዳን ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ዳይሬክተር ጄኔራል አብዱረህማን ጀማል ኢትዮጵያ ለሠላም ያላትን ዝግጁነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ የተመለከተው መሆኑን ገልጸው፤ "ሁለቱን አገሮች ወደለየለት ግጭት በማስገባት በአካባቢው ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሹ አካላት ፍላጎት አይሳካም" ብለዋል።
የድንበር ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ለሁለቱም አገሮች ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፤ በግጭት ለመፍታት መሞከር ለሱዳን ፋይዳ እንደሌለው ነው የተናገሩት።
"የሱዳን ጦር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁን የያዘውን ቦታ ለቆ በመውጣት ለዓለም አቀፍ ስምምነት ተገዥነቱን ማሳየት እና ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁነቱንና ቁርጠኝነቱን ማመላከት አለበት" ብለዋል።