ቀጥታ፡

በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የሚደግፉ መሆናቸውን የሀረማያ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

ሐረር፤ ኢዜአ ጥር 27/ 2013(ኢዜአ) ፡- ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጎን በመሆን በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የሚደግፉ መሆናቸውን በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሀረማያ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ መንግስት እያከናወነ ለሚገኘው የለውጥ ተግባር እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ሠላማዊ ሠልፍ አካሄደዋል።

ከሠልፈኞቹ መካከል ወጣት ዋርዮ መሐመድ በተለይ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጎን መሆናችንን እና በተለይ ስግብግቡ ጁንታ ላይ የተወሰደው  ህግ የማስከበር እርምጃን ለመደገፍ ሠልፍ ወጥተናል ብሏል።

በቀጣይም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻው እንደሚወጣ ተናግሯል።

የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚያካሂዱት የጁንታ ተላላኪዎች ተግባር በማውገዝ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያላቸውን ድጋፍና አክብሮት የገለጹት ደግሞ ሌላው የሠልፉ  ተሳታፊ ወይዘሮ ጂሃን አህመድ ናቸው።

ከዶክተር አብይ አህመድ ጎን በመሆን  በእሳቸው የሚመራውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

ወይዘሮ ሩሚያ ዩስፍ በበኩላቸው የዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ ጉዞ ለማሳካት የሚደግፉ መሆናቸውን ለመግለጽ  አደባባይ በመውጣት በሠልፉ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

የሀሰት ወሬ የሚያናፍሱ የማህበራዊ ትስስር ገፆችና ለጥፋት የሚያነሳሱ መገናኛ ብዙሃን  ተቀባይነት እንደሌላቸው ሊገነዘቡ እንደሚገባ  አመልክተዋል።

ሌላው የሠልፉ ተሳታፊ  አቶ አህመድ ሼህ መሐመድ ለውጡን  ያመጣው ጥቂት አካላት ሳይሆኑ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ  ብሔር ብሔረሰቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሠልፍ የወጡትም በብሔር ብሔረሰቦች ትግል የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠልና ለመደገፍ መሆኑን አመልክተው  ለስኬታማነቱም እገዛቸውን  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ ለሠልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ለውጡ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተገኘ ለውጥ ነው  ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ከከተማና ገጠር አካባቢ በመምጣት በዚህ የድጋፍ ሠልፍ መሳተፋቸው ለለውጡ መሳካት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ይህ ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በንቃት በመሳተፍ ማስቀጠል እንደሚኖርበትም መልዕክታቸውን  አስተተላልፈዋል።

የድጋፍ ሠልፉ በተመሳሳይ በምሥራቅ ሐረርጌ ጉርሱም፣ሜታ፣ቀርሳ፣ኮምቦልቻ፣ግራዋ ወረዳዎች እና አወዳይ ከተማ መካሄዱን ሪፖርተራችን ከሐረር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም