"አኖፌለስ ስቴፈንሳይ " የተሰኘች የወባ አስተላላፊ ትንኝ በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋች መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
"አኖፌለስ ስቴፈንሳይ " የተሰኘች የወባ አስተላላፊ ትንኝ በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋች መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27 / 2013 (ኢዜአ) "አኖፌለስ ስቴፈንሳይ" የተሰኘች የወባ አስተላላፊ ትንኝ በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋች መሆኑን የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ።
"አኖፌለስ ስቴፈንሳይ" በእስያ በከተሞች አካባቢ ወባን በማስተላለፍ የምትታወቅ የትንኝ ዝርያ ነች።
ለመጀመሪያ ጊዜ በፓኪስታን መገኘቷን የጀኔቲክ ጥናት እንደሚያመለክት መረጃዎች ያሳያሉ።
የትንኝ ዝርያዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምስራቅ የዓረብ ልሳነምድር እና በአፍሪካ ቀንድ አአገራት ከተሞች መገኘቷ በጥናት ተመላክቷል።
መራባት የምትመርጠው ቦታ ከተሞች አካባቢ መሆኑ ከሌሎች የወባ አስተላላፊ ትንኞች ልዩ ያደርጋታል፡፡
ህች ትንኝ በጅቡቲ፣ በሱዳንና በሶማሊያ የተገኘች ሲሆን በኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት በ2008 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ መገኘቷ ተረጋግጧል።
አሁኑ ወቅትም ወባ አስተላላፊ ትንኟ በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋች መሆኑ የተረጋገጠው በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ በዩ.ኤስ.አይ.ዲ ቪክተር ሊንክ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ በኔዘርላንድስ ሬድቦድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከልና በብሪታኒያ የለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጂን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲስን ትብብር በተካሄደ ጥናት ነው።
ጥናቱን በጤና ሚኒስቴር የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ 13 ከተሞች አዲስ የወባ በሽታ ተህዋስ አስተላላፊ ትንኟ እየተሰራጨች ነው።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ገነቱ እንዳሉት ወባ አስተላላፊዋ ትንኝ በሶሌ፣ በአፋር፣ በምስራቅ ኦሮሚያና ምስራቅ አማራ በሚገኙ ከተሞች መገኘቷ በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል።
ውሃ ገንዳዎች፣ በብሎኬት ማምረቻ አካባቢ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች፣ የፕላስቲክ እቃዎች ባለቀ የመኪና ጎማ ውስጥ በሚቀመጥ ውሃ፣ እርጥበት ባላቸውና ውሃ ባቆሩ አካባቢዎች በቀላሉ እንደምትራባ ገልፀዋል።
ኢንስቲትዩቱ የወባና ትኩረት የሚሹ የቆላማና ሐሩር በሽታዎች ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር እንዳላማው ጋይሳ ትንኟን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ስለባህሪዋና ሌሎች ጉዳዮች የመረጃ ልውውጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ጨማሪም "ለመንግስት አካላት መረጃ ማድረስና ማስረዳት፣ ከጎረቤት አገራት ጋር መረጃ መለዋወጥ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ትንኟን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የመነሻና የስርጭት ሁኔታዋን ለማወቅ ተከታታይ ጥናት ማካሄድና ለመራቢያ ምቹ አካባቢ እንዳታገኝ ማድረግ ይገባል" ያሉት ደግሞ በዩ.ኤስ.አይ.ዲ ቪክተርሊንክ የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኃላፊ ዶክተር መሸሻ ባልከው ናቸው።
ትንኟን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለጤና ባለሙያዎችና ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርት መስጠት እንደሚያሻም ጠቁመዋል።
ጥናቱ የምስራቅ አማራ አንዳንድ ከተሞችን ጨምሮ በሶማሌ ክልል ኤረር፣ ጂግጂጋ፣ ቀብሪደሃርና ጎዴ፤ በአፋር ክልል ሰመራ፣ ገዋኔና አዋሽ፤ በኦሮሚያ መተሃራ፣ ዝዋይ፣ መቂና ሞጆ ከተሞች እንዲሁም በድሬዳዋ ትንኟ መገኘቷንና ጥንቃቄ እንደሚያሻ አመላክቷል።