የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥራ ቋንቋዎችን ወደ 9 ሊያሳድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥራ ቋንቋዎችን ወደ 9 ሊያሳድግ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2013 (ኢዜአ) አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃ የሚያሰራጭባቸውን ቋንቋዎች ወደ 9 ሊያሳድግ ሲሆን በውጭ አገራትም ስምንት ቅርንጫፎችን ሊከፍት ነው።
ኢዜአ የአገር ውስጥ ቅርንጫፎቹንም ወደ 57 ሊያሳድግ መሆኑን አስታውቋል። ።
78 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢዜአ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ አገራዊ ተልዕኮ በመያዝ ዳግም በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፈጣን ለውጥ ላይ ይገኛል።
በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆን ራዕይ የሰነቀው ኢዜአ፤ በቀጣይ 10 ዓመታት የአገልግሎት ተደራሽነት በማስፋፋት በአገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች ተጠቃሽ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ፍኖተ ካርታ ነድፎ እየሰራ ነው።
በፍኖተ ካርታው ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ምክክር እንደተጠቀሰው አገልግሎት በሚሰጥባቸው የአገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን ወደ 9 ለማሳደግ አቅዷል።
በዚህም እስካሁ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ እንግሊዝኛና አረብኛ በተጨማሪ በትግረኛ፣ሶማሊኛ፣ ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ፣ሐረሪ፣ አፋርኛ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲሁም ስዋህሊና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ዜና እና ዜና ነክ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር ገልጿል።
ከነዚህም መካከል በትግርኛ ቋንቋ በቅርቡ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በፍኖተ ካርታው እንደጠቀሰው ሁለንተናዊ ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ዘመናዊ የስቱዲዮ ግንባታና የቅርንጫፍ ማስፋፊያ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም ተጠቁሟል።
በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊን ጉዳዮችን በመዳሰስ ተደራሽ ለመሆን በአገር ውስጥ ተጨማሪ 23 ቅርንጫፎችን በመክፈት ወደ 57 በማሳደግ፣ በውጭ አገራት ደግሞ 8 ወኪል ቅርንጫፎችን ለመክፈል ማቀዱን ኢዜአ አስታውቋል።