ቀጥታ፡

የወጡና በሂደት ላይ ያሉ ሕጎች ሲዘጋጁ የነበረን ሁኔታና ከሕጎቹ ጀርባ ያሉ ዓላማዎችን የሚያስረዳ መፅሀፍ ለሕትመት በቃ

ጥር /2013 (ኢዜአ) የወጡ ሕጎችና በሂደት ላይ የሚገኙ ሕጎች ሲዘጋጁ የነበረውን ሁኔታና ከሕጎቹ ጀርባ ያሉትን ዓላማዎች የሚያስረዳ መፅሀፊ ተዘጋጅቶ ለሕትመት በቅቷል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው መፅሃፍ ርዕስ "The Ethiopian law reform background document synopsis" ሲሰኝ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የፍትህ አክቲቪቲ ፕሮግራም ድጋፍ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

መፅሀፉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ተዘጋጅተው በተወካዮች ምክርቤት የፀደቁ 8 ህጎች፣  4 ረቂቅ እና 2 በመርቀቅ ሂደት ላይ የሚገኙ ሕጎችን የሚዳስስ ነው።

መፅሀፉን ምክትል ዓቃቤ ሕግ ገለታ ስዩም ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የፍትህ አክቲቪቲ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ዳግሊስ ተረክበዋል።

ምክትል ዓቃቤ ሕጉ መፅሀፉን ማዘጋጀት ያስፈለገው ባለፉት ሶስት ዓመታት በተቋሙ የረቀቁ ህግጋት ሲዘጋጁ የነበሩ ሂደቶችን፣ በህጎቹ ውስጥ ያሉ ድንጋጌዎችን ለመረዳትና ከህጎቹ ጀርባ ያለውን ትርጉምና ዓላማ ለማስረዳት ነው ብለዋል።

መፅሀፉ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያካሂዱም ሆነ ሕጎቹን ተግባር ላይ ለሚያውሉ አካላት ከፍያለ ጠቀሜታ እንዳለውም የገለጹት አቶ ገለታ መፅሀፉ ለህትመት እንዲበቃ ያገዙ አካላትን አመስግነዋል።

የፍትህ የአክቲቪቲ በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ዳግሊስ በበኩላቸው ለህትመት የበቃው መፅሀፍ ህጎች ሲዘጋጁ የነበሩ ሂደቶችን በሰነድ አዘጋጅቶ ተቋማዊ ተውስታ እንደኖራቸው ለማድረግ ነው ብለዋል።

መፅሀፉን ሕዝብ፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ህግ አውጪዎች ህጎች በሚወጡበት ጊዜ እንደ ማጠቀሻ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንደሆነ ተናግረዋል።

የፍትህ አክቲቪቲ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የሕግና የፍትህ ማሻሻያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል  ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።

መፅሀፉ በሶፍት ኮፕ ተዘጋጅቶ ለአንባቢያን ተደራሽ እንደሚሆን ተገልፃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም