ቀጥታ፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ እንደሚግፉ ገለጹ

ጥር 26/2013 (ኢዜአ) የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በአዲሱ አመራር የመጣውን አገራዊ ለውጥና ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያላቸውን ድጋፍ ዛሬ በአምቦ ከተማ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።

በአምቦ ከተማ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር በአገሪቷ እየተመዘገበ ያለውን የለውጥ ተግባር የሚያደንቁ ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት በዞኑ ህዝብ ላይ የተለያዩ በደሎችን ሲፈጽም በኖረው የህወሓት ቡድን ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊት የወሰደው እርምጃ  እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ከመንግስትና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

የአምቦ ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ ዋቁማ አዱኛ ባለፉት ዓመታት በህወሓት ቡድን የከተማው ህዝብ ከፍተኛ በደል ሲፈጸምበት እንደነበር አስታውሰው በተወሰደበት እርምጃ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሕዝቡ በመደማመጥ ችግሮች ለመፍታት ከመንግስት ጎን መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ከኤጀርሳ ለፎ ወረዳ በመምጣት በሰልፉ ላይ የታደመው ወጣት ደረጀ ብዙአየሁ በበኩሉ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የአገራችንን እድገት ማስቀጠል አለብን ሲል ተናግሯል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ሰልፈኞች በቀጣይ ካላፈው ስህተት በመማር ለአገር እድገት በአንድነት ከለውጡ አመራሮች ጎን መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።

አባ ገዳ ደጀኔ ደግሞ ህዝቡ የራሱን ሰላም በመጠበቅ መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ ማገዝ አለበት ብለዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ድሪብሳ ዋቁማ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ ባለፉት ዓመታት የጸረ ጭቆና ትግል ሲያካሂድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ህዝቡ በከፈለው መስዋዕትነት አገራዊ ለውጡ እንዲመጣ የበኩሉን መወጣቱንም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አንድነት የበለጠ እንዲጠናከርና እድገት እንዲመዘገብ መስራት አለበት ብለዋል።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ህዝብ በሚያጉላሉ ኃላፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

በመሆኑም ህዝቡ በራሱ መስዋዕትነት ያመጣውን ለውጥ በጽንፈኞች እንዳይነጠቅ መስራት ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም