ቀጥታ፡

ተርሚናሉ የተሽከርካሪ አገልግሎትን እንደሚያቀላጥፍና የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

ድሬዳዋ ፤ጥር 26/2013(ኢዜአ) የደወሌ የከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎች ማቆያ ተርሚናል ለወደብ በቅርበት መገንባቱ አገልግሎትን በማቀላጠፍና የስራ እድል በመፍጠር እንደሚጠቅማቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አሽከርካሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የተጠናቀቀው የደወሌ ተርሚናል በቅርቡ በተመረቀበት ወቅት የኢትዮጵያ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ማህበር አመራር አባል አቶ ዳመነ ተሾመ እንዳሉት ተርሚናሉ ለወደብ ቅርብ ከሆነው ጅቡቲ በቅርበት በመገንባቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

ተርሚናሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የቀሩ መሠረተ-ልማቶች ክፍተት እንዲስተካከል የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የፍሳሽ ጭነት ከባድ መኪና አሽከርካሪ አቶ አበበ ሞላ በበኩላቸው የተርሚናሉ መገንባት አሽከርካሪ ጅቡቲ ወረፋ ደርሶት እስኪጭን የሚያባክነውን ጊዜ ፣ ገንዘብና መንገላታት በማስቀረት እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል፡፡

ተርሚናሉ በሂደት እየተሟላ የሚመጣ ቢሆንም ለመሠረታዊ አገልግሎቶች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ሊሟሉለት ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡

የተርሚናሉ መገንባት ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጸችው ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ ወጣት አይሻ መሐመድ ናት፡፡

ወደፊት ተርሚናሉ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ቡና በማፍላት ሆነ በሌላም የገቢ ማስገኛ አማራጭ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግራለች፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ተደራጅተው በግንባታ ላይ የሥራ እድል ያገኙት አቶ አሸናፊ ደስታ በበኩላቸው በግንባታው ሂደት የስራ እድል በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ በሶስት ምዕራፍ የሚገነባው ተርሚናሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶች ግንባታን ጨምሮ ሌሎችም የቀሩ መሠረተ-ልማቶች የማሟላት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት በሚገኘው የሀገሪቱ ድንበር ከተማ ደወሌ ላይ የተገነባው የተርሚናሉ የመጀመሪያው ምዕራፍ በዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆን እና ከ71ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

ተርሚናሉ እስከ 500 ከባድ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችልም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም