ቀጥታ፡

ምርጫው በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

ደሴ፤ ጥር 26/2013(ኢዜአ )፡- ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ሁለት ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ መሃመድ ሻታ ለኢዜአ እንደተናገሩት  በምርጫው ለመሳተፍ አስፈላጊውን ቅደመ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡

ቅርንጫፋቸውን በተለያዩ ወረዳዎች በማስፋት ለውድድር የሚቀርቡ እጩ ተወዳዳሪዎችንም መምረጣቸውን አመልክተዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በሚያስቀምጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ለማስተዋወቅና የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግም ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ምርጫው ከበፊቱ በተለየ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ  ሆኖ እንዲጠናቀቅም የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ ደሴ ቅርንጫፍ ሊቀመንበር አቶ ዓይነቱ ኃይሉ በበኩላቸው ምርጫው ፍትሃዊና ሠላማዊ  ለማድረግ በሚከናወነው  እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ለመወጣት  ከአባላቶቻችና ደጋፊዎቻችን ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምርጫው የሚሳተፉ እጩ ተወዳዳሪዎችን መምረጣቸውንና አስፈላጊ ቅደመ ዝግጅትም እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ደንቦች፤ መምሪያዎችና ፖሊሲዎችም ግልጽ በሆነ መልኩ ተዘጋጅተዋል ያሉት አቶ ዓይነቱ ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ሃሳቡን ብቻ ለህዝብ በማቅረብ ለድርድር መቅረብ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ምርጫው ትክክለኛ እንዲሆንም ምርጫ ቦርድ ከታች እስከ ላይ የሚያዋቅራቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

መንግስትም የጀመረውን ምቹ መደላድል በመፍጠር  ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያሳየውን ቀና አመለካከት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ እስካሁን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅና ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ጠቁመው፤ በህገ ደንቡ መሰረት መስፈርቱን ያሟሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ እንዲሳተፉ መደረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።

''ሃገርና ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው ምርጫ ማድረግ የምንችለው'' ያሉት አቶ ዓይነቱ ለሀገር ሠላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩም  ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም